በክልሉ የተጀመረው የተቀናጀ የጤና ዘመቻ የሀሩራማ በሽታዎች መድኃኒት እደላን ያካተተ መሆኑ ተገለጸ
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የተጀመረውና ለ10 ቀናት የሚቆየው የተቀናጀ የጤና ዘመቻ የሀሩራማ በሽታዎች መድኃኒት እደላን ያካተተ መሆኑን በካርተር ሴንተር ኢትዮጵያ፤ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ገለጸ።
ህብረተሰቡ የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ጤንነቱን እንዲጠብቅ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤቱ አሳስቧል።
በክልሉ የኦንኮሰርኪያሲስ፣ የትራኮማ፣ የዝሆኔ እና ሌሎች በሽታዎችን ስርጭት ለመግታት እና ለመቆጣጠር ያለመ የተቀናጀ የ10 ቀናት የመድኃኒት እደላ እና የጤና ዘመቻ መጀመሩ ይታወሳል።
በክልሉ የካርተር ሴንተር ኢትዮጵያ የማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት የፕሮጀክት ማኔጀር አቶ ዮሐንስ እሸቱ እንደገለጹት፤ ዘመቻው የህብረተሰቡን ግንዛቤ ከማስፋት ጎን ለጎን የመድኃኒት ተደራሽነትን ያካተተ ነው።
አቶ ዮሐንስ አክለውም ካርተር ሴንተር በኢትዮጵያ ባለፉት 27 ዓመታት ከመንግሥት ጋር በመሆን የጊኒ ዎርም፣ ትራኮማ፣ ኦንኮሰርኪያሲስ እና የዝሆኔ በሽታዎችን ለመከላከል ሰፊ ሥራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን አስታውሰዋል።
ቀደም ሲል እነኚህ በሽታዎች ማህበረሰቡን ለከፍተኛ የጤና እክል ከመዳረጋቸውም በላይ ማህበራዊ ቀውስን ሲያስከትሉ እንደቆዪ በማስታወስ፤ በአሁኑ ወቅት በተከናወኑ የተቀናጁ ስራዎች በክልሉ አብዛኞቹ አካባቢዎች የማህበራዊ ስጋትነታቸው በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሱን ተናግረዋል።
በክልሉ የሚገኙ ሁሉም ወረዳዎችና የከተማ አስተዳደሮች ለኦንኮሰርኪያሲስ በሽታ ተጋላጭ ቢሆኑም በተደረጉ ዘመቻዎች የበሽታው ስርጭት በመቀነሱ በአሁኑ ወቅት በሽታው በላቦራቶሪ ምርመራ ብቻ ከመታወቁ ውጭ በአይን የሚታዩ የቁስለትና ሌሎች ምልክቶችን የማያሳይበት ደረጃ ላይ መድረሱ ተመላክቷል።
በተደረጉ የዳሰሳ ጥናቶች መሠረት በካፋ ዞን፤ አውራዳ ከተማ አስተዳደር፣ ዴቻ፣ ጎባ እና ጨታ ወረዳዎች ከበሽታው ነፃ መሆናቸውን የሚያመላክቱ ሁኔታዎች ታይተዋል ብለዋል።
በቤንች ሸኮ ዞን፤ በሰሜን ቤንች ወረዳ እንዲሁም በሸካ ዞን በሚገኙ ሁሉም ወረዳዎች ላይ አበረታች ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል።
በዓለም ጤና ድርጅት (WHO) መስፈርት መሠረት እነዚህን በሽታዎች እ.ኤ.አ. በ2030 ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት ታቅዶ እየተሰራ እንደሚገኝ የጠቆሙት አቶ ዮሐንስ፤ በሽታዎቹ በቁጥጥር ሥር በዋሉባቸው ወረዳዎች ላይ የሚሰጡ ሕክምናዎች ደረጃ በደረጃ የሚቆሙ መሆኑን አስረድተዋል።
ህብረተሰቡ የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም በአሁኑ ወቅት እየተካሄደ ባለው ዘመቻ መድኃኒቶችን በመውሰድ ጤንነቱን እንዲጠብቅ አቶ ዮሐንስ ጥሪ አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ፡ ትዕግስቱ ጴጥሮስ – ከቦንጋ ጣቢያችን

More Stories
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት የክልሉን መንግስት የ2019 በጀት ከ85.7 ቢሊየን ብር በላይ አፀደቀ
በክላስተር ቴክኖሎጂ በመዝራት የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ በትጋት እየተሰራ እንደሚገኝ የከምባታ ዞን ግብርና መምሪያ አስታወቀ
ለፍትሕ ተቋማት ምቹ አካባቢን መፍጠር ለተሻለ ፍትህና ቀልጣፋ አገልግሎት ጉሊህ ሚና ያለው መሆኑ ተገለፀ