ለፍትሕ ተቋማት ምቹ አካባቢን መፍጠር ለተሻለ ፍትህና ቀልጣፋ አገልግሎት ጉሊህ ሚና ያለው መሆኑ ተገለፀ

ለፍትሕ ተቋማት ምቹ አካባቢን መፍጠር ለተሻለ ፍትህና ቀልጣፋ አገልግሎት ጉሊህ ሚና ያለው መሆኑ ተገለፀ

በከምባታ ዞን ዶዮገና ከተማ አስተዳደር በ12.7 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በህብረተሰብ ተሳትፎ የሚገነባ የፖሊስ ተቋም ህንጻ ለመገምባት የመሠረት ድንጋይ ጥሏል።

በመርሀ-ግብሩ ላይ ተገኝተው የመሠረት ድንጋይ ያስቀመጡት የዶዮገና ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ግሩም ወ/ማሪያም እንደገለጹት፤ ለህብረተሰቡ የተሻለ ፍትህ ተደራሽ ለማድረግ እና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ለፍትሕ ተቋማት ምቹ አካባቢን መፍጠር ጠቀሜታቸው የጎላ ነው።

ግንባታዉ በአጭር ጊዜ ተገንብቶ ለአገልግሎት ክፍት እስከሚሆን ድረስ የጋራ ርብርብ እንደሚደረግ ገልፀዋል።

የከተማው ነዋሪዎችና ባለሀብቶች ለከተማው እድገት ከፍተኛ ድጋፍ እያደረጉ መቆየታቸውን አውስተው፤ ህብረተሰቡ አሁንም የተለመደውን ትብብር አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።

የዶዮገና ከተማ አስተዳደር ፖሊስ አዛዥ ሻላቃ ሙላቱ ተስፋዬ በበኩላቸው፤ ተቋማቸው በኪራይ ቤት ከመሆንም በላይ ምቹ አካባቢ ያለመኖሩን አንስተው የህንጻ ግንባታው የወንጀል ተጠርጣሪዎች በሰላማዊ ሁኔታ በቂ ቦታ ውስጥ እንዲቆዩ ከማድረግም ባለፈ የወንጀል ማስረጃዎች እና መዝገቦች ከአደጋ ተጠብቀው ተደራጅተው እንዲቀመጡ ያግዛል ብለዋል።

ከወር ደመወዝ መዋጮ ጀምሮ አባላት በፍቃደኝነት የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ዋና አዛዡ ገልፀዋል።

የህዝብን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅና ለፖሊስ ቅንጅታዊ አሰራር የተደራጀ ቢሮ ወሳኝ ነው ያሉት ደግሞ የከተማ አስተዳደሩ ሠላምና ፀጥታ ጽ/ቤት ኃላፊ ዋና ሳጅን ሳሙኤል ጌታሁን ናቸው።

የፖሊስ አባላቱ ግንባታው ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ የድርሻቸውን እንደሚወጡ የገለፁ ሲሆን በዕለቱም ከ7 መቶ ሺህ በላይ ብር ጥሪ ከተደረገላቸው አካላት ቃል ተገብቷል።

የግንባታው አጠቃላይ ወጪ 12.7 ሚሊዮን ብር በላይ መሆኑ ተመላክቷል።

ዘጋቢ: መልካሙ ታፈሰ – ከሆሳዕና ጣቢያችን