የገቢ ሴክተር ከመንግስትና ከህዝብ የተሰጠውን ተልዕኮ ለመወጣት ታክስን በባለቤትነት በመሰብሰብ ፈጣን ልማት እንዲረጋገጥ የድርሻውን ሀላፊነት በመወጣት ላይ አንደሚገኝ የጉራጌ ዞን ገቢዎች መምሪያ ገለፀ

የገቢ ሴክተር ከመንግስትና ከህዝብ የተሰጠውን ተልዕኮ ለመወጣት ታክስን በባለቤትነት በመሰብሰብ ፈጣን ልማት እንዲረጋገጥ የድርሻውን ሀላፊነት በመወጣት ላይ አንደሚገኝ የጉራጌ ዞን ገቢዎች መምሪያ ገለፀ

መምሪያው የ2018 በጀት አመት የገቢ እቅድ አፈፃፀም ላይ ከሴቶችና ወጣቶች አደረጃጀት፣ እንዲሁም ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር የዜጎች ቻርተር ጽንሰ-ሀሳብ ላይ የውይይት መድረክ በወልቂጤ ከተማ አካሂዷል፡፡

መድረኩን በንግግር የከፈቱት የጉራጌ ዞን ገቢዎች መምሪያ ሃላፊ አቶ ሚነወር ሃያቱ እንዳሉት፤ ተቋማቸው ከህዝብና ከመንግስት የተሰጠውን ተልዕኮ ለመወጣት የገቢ ሴክተር ታክስን በመሰብሰብ ፈጣን ልማት እንዲረጋገጥ የድርሻውን ሀላፊነት በመወጣት ላይ ይገኛል።

በዞኑ በ2018 በጀት አመት ለመሰብሰብ ከታቀደው 4 ቢሊዮን 818 ሚሊዮን 14 ሺህ 262 ብር ውስጥ 4 ቢሊዮን 798 ሚሊዮን 840 ሺህ 389 ብር በመሰብሰብ የእቅዱን 99 ነጥብ 64 በመቶ ማሳካት ተችሏል ብለዋል አቶ ሚነወር።

አያይዘውም መምሪያው በ2019 በጀት አመት ላይ ከተለያዩ የገቢ አርዕስቶች 6 ቢሊዮን 149 ሚሊዮን 607 ሺህ 903 ብር ለመሰብሰብ አቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን ገልጸዋል።

መምሪያው በ2018 በጀት አመት ከገጠሙት ችግሮች ውስጥ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ደረሰኝ በተገቢው መንገድ ያለመስጠት፣ በኢንቨስትመንት ስራ ላይ የተሰማሩ አካላት የሠራተኞችን ግብር በወቅቱ ያለመክፈል እንደሚገኙበት በመድረኩ ላይ አቶ ሚነወር አንስተዋል።

አክለውም በዞኑ አንዳንድ ታክስ የማይከፍሉ የግል ትምህርት ቤቶች መኖራቸውን ያወሱት ሃላፊው፤ በቀጣይ ትምህርት ቤቶቹ ሀገር ተረካቢ ትውልድ ከመቅረጽ ባሻገር ለመንግሥት የሚገባውን ግብር በውቅቱ መክፈል እንደሚገባቸው አሳስበዋል።

በበጀት ዓመቱ ከደረጃ (ሀ) ግብር ከፋዮች 108 ሚሊየን 932 ሺ 638 ብር መሰብሰቡንና ከ497 የደረጃ (ለ) ግብር ከፋዮች 12 ሚሊየን 405 ሺህ ብር ተሰብስቧል፡፡

17 ሺህ 441 የደረጃ (ሐ) ግብር ከፋዮች ግብርና ታክሳቸውን የከፈሉ ሲሆን በዚህም 78 ሚሊየን ብር ገቢ ተገኝቷል ሲሉ ገልጸዋል ሀላፊው፡፡

አያይዘውም በበጀት አመቱ ግብይትን በደረሰኝ በማይፈጽሙና የታክስ ህግን በሚተላለፉ ግብር ከፋዮች ላይ ህጋዊ እርምጃ መወሰዱን አብራርተዋል።

በመድረኩ ላይ የመወያያ ሰነድ ያቀረቡት የጉራጌ ዞን ገቢዎች መምሪያ የእቅድ ዝግጅት አፈጻጸም ክትትል ለውጥ ስራ አመራርና መረጃ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ክፍሉ ኬርጋ፤
በመምሪያው በ2018 በጀት ዓመት የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያጎለብቱ ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውን ተናግረዋል።

በተለይም ለዞኑ ልማት የሚውል ገቢ በተገቢው መሰብሰብ አንዲቻል ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች በማሳተፍ በተሰራው ስራ በአመቱ የተሻለ ታክስ መሰብሰቡን አብራርተዋል።

ተቋሙ አምስት የትኩረት መስኮችና 15 ግቦችን በመያዝ ውጤት ተኮር ስራ እየሰራ እንደሆነ የገለፁት አቶ ክፍሉ፤ ይህንኑ በማጠናከር በበጀት አመቱ የግብር አከፋፈል ስርዓቱን ለዜጎች ምቹ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል።

አሁን ላይ የታክስ ሌብነትን በመዋጋት የብልሹ አስራር ምንጩን ለማድረቅ ከፍርድ ቤቶች ጋር ከየትኛውም ጊዜ በላቀ መልኩ በቅንጅት እንደሚሰሩ በመድረኩ ላይ ተጠቁሟል።

በመድረኩ ላይ ያነጋርናቸው ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት በ2018 በጀት አመት ወደ ታክስ መክፈል ማዕቀፍ ውስጥ ያልገቡ ነጋዴዎች በተቀናጀ መልኩ ማስገባት አንደሚገባ ተናግረዋል።

እንደ አስተያየት ሰጪዎቹ ገለፃ የደረሰኝ ጉዳይ የነጋዴው ችግር ብቻ ሳይሆን ማህበረሰቡ ደረሰኝን ጠይቆ ከመውሰድ ጋር ተያይዞ ውስንነቶች በመኖራቸው በዚህ ዙሪያ ለሚመለከተው ሁሉ ግንዛቤ መፈጠር እንደሚገባም አብራርተዋል።

ዘጋቢ፡ ደጋጋ ሂሳቦ – ከወልቂጤ ጣቢያችን