የመተጋገዝና የመረዳዳት ባህላችንን በማጎልበት ድጋፍ የሚሹ ወገኖችን ማገዝ እንደሚገባ ተገለጸ
ሀዋሳ፡ ሐምሌ 17/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የመተጋገዝና የመረዳዳት ባህላችንን በማጎልበት ድጋፍ የሚሹ ወገኖችን ማገዝ እንደሚገባ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ ሀላፊ አቶ ሙስጠፋ ኢሳ ገለጹ፡፡
ቢሮው የ2018 ዓ.ም የክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በቀቤና ልዩ ወረዳ በፈቃዶ ቀበሌ የአንዲት አረጋዊን ቤት በአዲስ መልክ ግንባታ ማስጀመሪያ መርሃ-ግብር አከናውኗል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ ሀላፊ አቶ ሙስጠፋ ኢሳ በዚህ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፤ በጎነት ከልብ የሚመነጭ መሆኑን ተከትሎ በራስ ተነሳሽነት የሚከናወን ተግባር ነው።
በተለይም ከለውጡ ወዲህ በዘርፉ በተከናወኑ ተግባራት በርካታ ወገኖች ተጠቃሚ መሆናቸውን የገለጹት ሃላፊው፤ የመተጋገዝና የመረዳዳት ባህላችንን በማጎልበትና ያሉን አቅሞችንና ጸጋዎችን በማስተባበር ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች አጋዥ መሆን አለብን ሲሉ ተናግረዋል።
ብልጽግና ፓርቲ ሰው ተኮር መሆኑን ተከትሎ በራስ አቅም በመረዳዳት፣ አቅም ለሌላቸው አቅም በመሆን በተግባር እያረጋገጠ ይገኛል ብለዋል።
በዚህ መነሻነትም ቢሮው በልዩ ወረዳው በመገኘት የአንዲት አረጋዊን ቤት በአዲስ መልክ ግንባታ የማስጀመር፣ የአረንጓዴ አሻራ ማኖርና ድጋፍ ለሚሹ ህፃናት የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን አመላክተዋል። የሚገነባው ቤትም በአጭር ጊዜ ውስጥ ቢሮው ሰርቶ እንደሚያስረክብ ገልጸዋል።
እንደ ሀገር የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኝ በማንሳት ከነዚህ መካከልም የመረዳዳትና የመደጋገፍ በጎ እሴቶችን በዘላቂነት ውጤታማ ማድረግ አንዱ በመሆኑ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በዘርፉ እያደረጉት ያለውን ተሳትፎ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።
ቢሮው የአካባቢ ጸጋዎችን በመለየት ስራ ፈላጊዎችን ስራ እንዲያገኙ በማድረግ ዘርፈ ብዙ ስራ እየሰራ እንደሚገኝ በመጠቆም የልዩ ወረዳው ወጣቶችም በአካባቢው ሰርቶ መለወጥ እንደሚቻል በተግባር ማሳየት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የቀቤና ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሃመድ አሚን በደዊ፤ ቢሮው በልዩ ወረዳው በመገኘት ላከናወነው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባር ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ሀገር በትብብር እንደምትገነባ ጠቅሰው፤ በተለይም የለውጡ መንግስት የመረዳዳትና የመደጋገፍ በጎ እሴቶች እንዲጎለብቱ በማድረጉ የህዝቡ ተጠቃሚነት እያደገ መምጣቱን አመላክተዋል።
በልዩ ወረዳው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራት የአቅመ ደካሞች ቤቶችን ከመገንባት ጀምሮ የተለያዩ ዘርፎች በትኩረት እየተከናወኑ እንደሚገኙ የገለፁት ዋና አስተዳዳሪው፤ ማህበረሰቡ በዘርፉ እያደረገ የሚገኘውን ድጋፍና ተሳትፎ አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ተናግረዋል።
የልዩ ወረዳው ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ካፉ አረቦ በበኩላቸው፤ በልዩ ወረዳው የዘንድሮው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት በማድረግ ወደ ተግባር ተገብቷል ነው ያሉት።
አሁን ላይ ተግባሩ በ16 ዋና ዋና ዘርፎች እየተከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ ተግባሩ በውጤታማነት በመፈጸም በቀጣይ የበጋ ወራትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
በልዩ ወረዳው የፈቃዶ ቀበሌ ነዋሪዋ ወ/ሮ ጡበቴ ሼህ ሳሊህ አቅመ ደካማና ጧሪም ደጋፊም የሌላቸው ከመሆኑ የተነሳ በፈራረሰ ቤት ክረምት በመጣ ቁጥር ዝናብና ብርድ ይፈራረቅባቸው እንደነበረ ገልፀው፤ መንግስት ላደረገላቸው ድጋፍ አመስግነዋል።
የወ/ሮ ጠብቴ ሼህ ሳሊህ ጎረቤት የሆኑት አቶ ፈቱ ሸምሱ ግለሰቧ በተጎሳቆለ ቤት ዝናብና ፀሀይ ሲፈራረቅባቸው ተቋቁመው ያለረዳት ይኖሩ እንደነበረ ምስክርነታቸውን የሰጡ ሲሆን ለተደረገላቸው መልካም ተግባር መደሰታቸውን አስረድተዋል።
“በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ቃል እየተከናወነ በሚገኘው በዚህ ተግባር ላይ ከቢሮውና ከልዩ ወረዳው የተውጣጡ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችና ባለሙያዎች እንዲሁም ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።
ዘጋቢ፡ መሀመድ ሽሁር – ከወልቂጤ ጣቢያችን

More Stories
ወባን ጨምሮ ሌሎች የማህበረሰብ ጤና ችግሮችን ለመከላከል በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ
የክረምት በጎ ተግባራት አቅመ ደካሞችን ከዝናብና ፀሐይ ለመጠለል ከማገዝ ባሻገር የአቅመ ደካሞችን የመኖር ተስፋ የሚያለመልም መሆኑ ተገለጸ
ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ኢትዮጵያን ወደ ቀደምት ከፍታዋ ለመመለስ ጉልህ ሚና ይጫወታል – በጌዴኦ ዞን የይርጋጨፌ ከተማና አካባቢዋ ነዋሪዎች