ወባን ጨምሮ ሌሎች የማህበረሰብ ጤና ችግሮችን ለመከላከል በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ
ሀዋሳ፡ ሐምሌ 17/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) ወባን ጨምሮ ሌሎች የማህበረሰብ ጤና ችግሮችን ለመከላከል በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የጎፋ ዞን ጤና መምሪያ ገለጸ፡፡
መምሪያው የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸም ግምገማና የ2019 በጀት ዓመት ጠቋሚ ዕቅድ ላይ የውይይት መድረክ አካሂዷል።
በመድረኩ የተገኙት የጎፋ ዞን ምክትል ዋና አስተዳዳሪና የሥራና ክህሎት መምሪያ ኃላፊ አቶ ምናሴ ኤልያስ፤ በ2018 በጀት ዓመት የጤና ተቋማትን የማስፋፋትና የግንባታ ሥራዎች በቅንጅት በመከናወናቸው ተጠናቀው ለአገልግሎት መብቃታቸውን ገልጸዋል።
በተመሳሳይም የመድኃኒት አቅርቦት እጥረት በቀጣይ ሊፈታ እንደሚገባ አሳስበዋል።
አቶ ምናሴ በአንዳንድ የዞኑ አካባቢዎች የተከሰተውን የወባ ወረርሽኝ ለመቆጣጠር የማህበረሰቡ ንቁ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፤ በተለይም የእናቶች የወሊድ አገልግሎት ዙሪያ የግንዛቤ ሥራ ሊጠናከር እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
የጎፋ ዞን ጤና መምሪያ ምክትል ኃላፊ ሲስተር አሚናት ሰይድ በበኩላቸው፤ የ2018 በጀት ዓመት የጤና ዘርፉ አፈጻጸም ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የተሻለ ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል።
በተጨማሪም በአንዳንድ ወረዳዎች እየተስፋፋ የሚገኘውን የወባ ወረርሽኝ ለመከላከልና ሕሙማንን በፍጥነት ለማከም እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
የበሽታውን ስርጭት በዘላቂነት ለመቀነስ ማህበረሰቡ የአካባቢ ንጽህናን እንዲጠብቅና የወባ መከላከያ አጎበርን በአግባቡ እንዲጠቀም ጥሪ አቅርበዋል።
በመድረኩ የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸም ሪፖርትና የ2019 በጀት ዓመት ጠቋሚ ዕቅድ ቀርቦ ውይይት ተካሂዷል።
ተሳታፊዎችም በዞኑ የወባ መከላከል፣ የእናቶች የወሊድ አገልግሎት ማሻሻልና የደም እጥረት ችግርን መቀነስ በቀጣይ የልዩ ትኩረት መስኮች እንደሚሆኑ ገልጸዋል።
ዘጋቢ፡ ስንታየሁ ሙላቱ – ከሳውላ ጣቢያችን

More Stories
የመተጋገዝና የመረዳዳት ባህላችንን በማጎልበት ድጋፍ የሚሹ ወገኖችን ማገዝ እንደሚገባ ተገለጸ
የክረምት በጎ ተግባራት አቅመ ደካሞችን ከዝናብና ፀሐይ ለመጠለል ከማገዝ ባሻገር የአቅመ ደካሞችን የመኖር ተስፋ የሚያለመልም መሆኑ ተገለጸ
ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ኢትዮጵያን ወደ ቀደምት ከፍታዋ ለመመለስ ጉልህ ሚና ይጫወታል – በጌዴኦ ዞን የይርጋጨፌ ከተማና አካባቢዋ ነዋሪዎች