የክረምት በጎ ተግባራት አቅመ ደካሞችን ከዝናብና ፀሐይ ለመጠለል ከማገዝ ባሻገር የአቅመ ደካሞችን የመኖር ተስፋ የሚያለመልም መሆኑ ተገለጸ

የክረምት በጎ ተግባራት አቅመ ደካሞችን ከዝናብና ፀሐይ ለመጠለል ከማገዝ ባሻገር የአቅመ ደካሞችን የመኖር ተስፋ የሚያለመልም መሆኑ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ሐምሌ 17/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የክረምት በጎ ተግባራት አቅመ ደካሞችን ከዝናብና ፀሐይ ለመጠለል ከማገዝ ባሻገር የአቅመ ደካሞችን የመኖር ተስፋ የሚያለመልምም ጭምር ነው ሲሉ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዲላሞ ኦቶሬ ዶ/ር ገለፁ።

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የ2018 የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ማስጀመሪያ መርሀ ግብር ለ6 አቅመ ደካማ ወገኖች የመኖሪያ ቤት ግንባታ ማስጀመሪያ መርኃ ግብር በሆሳዕና ከተማ ሊች አምባ ቀበሌ አካሄዷል፡፡

በመርሀ ግብሩ የተገኙት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ ዲላሞ ኦቶሬ (ዶ/ር) የፌዴራል ቡናና ሻይ ባለስልጣን ለአቅመ ደካማ ወገኖች በሆሳዕና ከተማ አስተዳደር 6 ቤቶችን እንደሚገነባ ጠቁመው በክልሉ ይህን ጨምሮ በዘንድሮ ዓመት ከ2 ሺ በላይ የአቅመ ደካማ ቤቶች በገጠርም በከተማም የሚገነቡ መሆኑን ገልፀዋል።

የቤቶቹ መገንባት ከዝናብና ፀሐይ ለመጠለል ከማገዝ ባሻገር መንግስትና ህዝብ ለአቅመ ደካሞች ከጎናቸው መሆኑን የሚያመላክትና የአቅመ ደካሞችን የመኖር ተስፉ የሚያለመልም ጭምር ነው ብለዋል።

ዶክተር ዲላሞ አክለውም፤ በዘንድሮው የክረምት በጎ ተግባራት በክልሉ ከ2.5 ሚሊየን በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ ከ4 ቢሊየን ብር በላይ ገንዘብ ለማዳን ታቅዶ ወደ ስራ የተገባ መሆኑን አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) ተቋሙ የበጎ አድራጎት ስራዎችን በተለያዩ አካባቢዎች በየዓመቱ እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ በዘንድሮ ዓመትም ከ2 እስከ 3 ሚሊየን ገንዘብ በጀት በመመደብ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሆሳዕና ከተማ 6 የአቅመ ደካማ ቤቶችን ለመገንባትና ከዛም ባሻገር ለ1 ሺ ተማሪዎች የሚሆን የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጋቸውን አመላክተዋል።

ይህም ኢትዮጵያዊ የመደጋገፍ እሴትን ይበልጥ የሚያጎላ መሆኑን በመጠቆም የቤቶቹን ግንባታ ስራም ከሁለት እስከ ሶስት ወራት ባሉ ጊዜያት ውስጥ አጠናቆ ለማስረከብ መታቀዱን አመላክተዋል።

የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሽጉጤ በበኩላቸው፤ በከተማ አስተዳደሩ በተለዩ 16 የስራ ዘርፎች በጎ አድራጊዎችን በማሳተፍ ለመስራት ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን ጠቁመው የፌዴራል ቡናና ሻይ ባለስልጣን በበጎ ተግባራቱ በመሳተፍ የሚያደርገው ተግባር የዘንድሮውን የክረምት በጎ ተግባር ልዩ እንደሚያደርገውና ይህም የሚበረታታ መሆኑን ገልፀዋል።

ድጋፍ የተደረገላቸው የህብረተሰብ ክፍሎችም በተደረገላቸው ድጋፍ ደስተኞች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በመርሀ ግብሩ የፌዴራል፣ የክልል፣ የዞንና የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር በየደረጃው ያሉ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

ዘጋቢ: አማኑኤል አጤቦ – ከሆሳዕና ጣቢያችን