‎ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ኢትዮጵያን ወደ ቀደምት ከፍታዋ ለመመለስ ጉልህ ሚና ይጫወታል – በጌዴኦ ዞን የይርጋጨፌ ከተማና አካባቢዋ ነዋሪዎች

‎ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ኢትዮጵያን ወደ ቀደምት ከፍታዋ ለመመለስ ጉልህ ሚና ይጫወታል – በጌዴኦ ዞን የይርጋጨፌ ከተማና አካባቢዋ ነዋሪዎች

‎ሀዋሳ፡ ሐምሌ 17/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ኢትዮጵያ ወደ ቀደም ከፍታዋ እንድትመለስ ጉልህ ሚና እንደሚያበረክት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጌዴኦ ዞን የይርጋጨፌ ከተማ አስተዳደርና አካባቢዋ ነዋሪዎች ገለጹ።

‎ኢትዮጵያ የውስጥ ችግሯን በራስ አቅም በመፍታት የጋራ መግባባትን ለመፍጠር እየወሰደች ያለችውን እርምጃ በደስታ እንደሚደግፉ ነው በዞኑ የይርጋጨፌ ከተማና አካባቢዋ ነዋሪዎች የተናገሩት።

‎አስተያየታቸውን ለደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ይርጋጨፌ ቅርንጫፍ የሰጡት የከተማዋና አካባቢዋ ነዋሪዎች መካከል አቶ ተስፋዬ ባንቶላ፣ ወይዘሮ የምስራች ብርሃኔ እና ሌሎችም፤ በብዙ ህብረ ቀለማት ያጌጠው የኢትዮጵያ ምድር ከዓለት በጠነክረ ውስጣዊ አንድነቱ በሚታወቅና የአይበገሬነት ወኔ መገለጫው በሆነ ህዝብ ዙሪያዋ የታጠረ መሆኑን አስረድተዋል።

‎ይህም የመደማመጥና ከዳር እስከ ዳር ለአንድነት የመቆም ጠንካራ ባህል በየጊዜው ከሚነሱ የውስጥና የውጪ ጠላቶች ኢትዮጵያን በመታደግ ለፈተና የማትበገር ሀገር ሆና እንድትቆይ እንዳስቻላት ነው ነዋሪዎቹ ያብራሩት።

‎ይህን በታላቅ የደምና ነፍስ መስዋዕትነት ጸንታ የኖረችን ሀገር ለማናጋት ታሪክን የሚያዛቡ፣ በሀይማኖቶች መካከል ልዩነቶችን የሚሰብኩ፣ በፖለቲካ ሽኩቻ ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር ሌት ተቀን የሚሠሩ አካላት ዓላማቸው ባይሰምርም በርካታ ውድመቶችን ማስከተሉን አስታውሰዋል።

‎ጠልፎ በመጣልና በህዝብ መካከል የጦርነት ነጋሪትን በመጎሰም የሚመጣ አሸናፊነትም ሆነ የተረጋጋ ሰላም አለመኖሩን ለማሳየት የተወሰደው በውይይት ችግሮችን የመፍታት ጥበብ የሚደነቅና ኢትዮጵያን ወደ ቀደምት ከፍታዋ እንድትመለስ ከፍተኛ ሚና የሚጫወት መሆኑን አስረድተዋል።

‎በመሆኑም ሁሉም ለምክክሩ ስኬት የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ የጠየቁት ነዋሪዎቹ፤ ከምክክሩ በኋላ ዜጎች ያለ ስጋት የሚንቀሳቀሱባትን፣ የተረጋጋ ሰላምና ዘላቂ ልማት የሚረጋገጥባትን፣ የትናንቱ መደማመጥና መከባበር መለያዋ የሆነችውን ኢትዮጵያን በድጋሚ እንደሚያዩ ባለ ሙሉ ተስፋ መሆናቸውን ተናግረዋል።

‎ዘጋቢ: ሳሙኤል በቀለ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን