የጤና አገልግሎትንና የመድኃኒት አቅርቦትን በቴክኖሎጂ ለማዘመን የሚያስችል የመድሐኒት ልየታና ምዝገባ መካሄድ ጀመረ

የጤና አገልግሎትንና የመድኃኒት አቅርቦትን በቴክኖሎጂ ለማዘመን የሚያስችል የመድሐኒት ልየታና ምዝገባ መካሄድ ጀመረ

ሀዋሳ፡ ሐምሌ 17/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የሲዳማ ክልል ጤናና ጤና ነክ አገልግሎትና ግብዓት፣ ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን ጤንነቴ (Teninete) የተሰኘ የሞባይል መተግበሪያ ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችለውን አሰራር በመዘርጋት በሀዋሳ ከተማ የሚገኙ መድሀኒት ቸርቻሪ ተቋማት ባለንብረቶች ያላቸውን መድሐኒት ለይቶና መዝግቦ ከሲስተም ጋር የማስተሳሰር ተግባራዊ ስራ መጀመሩን አስታወቀ፡፡

በሀዋሳ ከተማ የሚገኙ መድሐኒት ቤቶች በስቶካቸው የሚገኙ መድሐኒቶችን ለይተውና መዝግበው ጤንነቴ (Teninete) በተሰኘ የሞባይል መተግበሪያ ሲስተም ላይ በመጫን የተጠቃሚዎችን ጊዜ እና ጉልበት በመቆጠብ በዘመነ የዲጂታል አሰራር ውስጥ ማለፍ እንዳለባቸው የባለሰልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ቡሪሶ ቡላሾ አስረድተዋል፡፡

የትኛውም በክልሉ የሚገኝ መድሐኒት ቤት ያለቸውን መድሐኒት መዝግበው፥ ምን አይነት መድሐኒት የት መድሐኒት ቤት አለ? የሚለውን በያዙት ስልክ በጤንነቴ መተግበሪያ አማካኝነት በቀላሉ ጊዜና ጉልበት እንዲሁም ተጨማሪ ወጪ ሳያወጡ መድሐኒቱን ማግኘት የሚያስችል አሳራር እየተዘረጋ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የጤና አገልግሎትንና የመድኃኒት አቅርቦትን በቴክኖሎጂ ለይቶና መዝግቦ ለተጠቃሚዎች ለማድረስ በዛሬው እለት ያሉትን መድሐኒቶች መዝግበው ወደ ኮምፒውተር ላይ የመጫን ስራ እየተሰራ መሆኑን የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሩ፥ የመድሐኒት መደብር ባለቤቶች፣ ቴክኒካል ማናጀሮች፣ የአይ.ሲ.ቲ ባለሙያዎችን ያቀፈ 10 ቡድን በሀዋሳ በሚገኙ 257 የመድሐኒት መደብሮች ላይ የምዝገባ ሂደቱን እያከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ቀደም ሲል አንድ ታካሚ የታዘዘለትን መድሃኒት በአንድ መድሐኒት መደብር ቢያጣ ወደ ሌላ በመዘዋወር ፈለጎ ማግኘት ይጠበቅበት የነበረውን የተንዛዛና አድካሚ ችግር በመፍታት፥ በሞባይል የጤንነቴ መተግበሪያ በመጠቀም ብቻ የሚፈልገው መድሐኒት የት መደብር እንደሚገኝ በቀላሉ ማግኘት የሚያስችል አሰራር መፈጠሩን ተናግረዋል፡፡

ሕብረተሰቡ ያለ እንግልት የታዘዘለትን መድኃኒት ከየት ማግኘት እንደሚችል እንዲያውቅ ለማስቻል ሁሉም የመድሐኒት መደብሮች ያላቸውን መድሐኒት ለይተውና መዝግበው በአንድ ቀን ተኩል ጊዜ ውስጥ ማጠናቀቅ እንዳለባቸው ዋና ዳይሬክተሩ አሳስበዋል፡፡

የአፍሪካ መድሐኒት መደብር ባለቤት አቶ ግርማ ተፈራ በዚህ ወቀት በሰጡት አስተያየት የጤና ተቋማት የመድኃኒት ግብይትና አስተዳደር በዲጂታል እንዲመራ መደረጉ ያለውን አዎንታዊ ጎን ገልጸው፥ አሁን ያለውን የአገልግሎት ጥራትን ያሻሽላል ብለዋል።

ህብረተሰቡም በቀላሉ የታዘዘለትን መድሐኒት በቀላሉ እንዲያገኝ የሚያግዘው በመሆኑ እንዲህ አይነት አሰራር መጀመሩ ሆሉንም ወቀገን ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ የኤልሮኢ መድሐኒት መደብር ረዳት ባለሙያ አቶ ደሳለኝ ዳንጉራ የጤንነቴ መተግበሪያ አጠቃቀምና ቴክኒካል ነገሮች ላይ በቂ እውቀት እንዲጨብጡ መደረጉን ጠቁመው አጠቃቀሙም ቀላልና ለህብረተሰቡም ያለው ጥቅም ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡

ዘጋቢ፡ ዘላለም ተስፋዬ