ሙስና የሚያስከትለውን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ቀውስ መታገል እንደሚገባ ተገለጸ
በቡርጂ ዞን የባለድርሻ አካላት የፀረሙስና ውይይት መድረክ ተካሂዷል።
በሀገራችን ለ24ኛ፣ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ደረጃ ደግሞ ለ23ኛ ጊዜ የሚከበረው የፀረ ሙስና ቀን በዞኑ “ስውር ትስስሮችን በማጋለጥ ሙስና መሰል ወንጀሎችን እንበጣጥስ” በሚል መሪ ቃል ይከበራል።
በቡርጂ ዞን ፋይናንስ እና ኢኮኖሚ ልማት መምሪያ የፀረሙስና ቡድን መሪ አቶ ኦቴ ሀልቻዬ
እንደ ሀገር ለ24ኛ፣ በክልል ደረጃ ደግሞ ለ23ኛ ጊዜ የሚከበረውን የፀረሙስና ዕለት አስመልክቶ ሙስና በሀገር ኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ እድገት ላይ ያለውን አሉታዊ ተጽዕኖ ህብረተሰቡ በተገቢው እንዲገነዘብ የማድረጉ ሥራ እንደሚከናወን አስረድተዋል።
ዕለቱ በሶያማ ከተማ እና ዙሪያ ወረዳ አስቀድሞ በተለያዩ ኩነቶች ሲከበር ቆይቶ ህዳር 23 ቀን 2019 ዓ.ም በዞን ደረጃ የማጠቃለያ መርሀ ግብር እንደሚካሄድ የጠቆሙት አቶ ኦቴ፤ በበዓሉ ወቅት የመንግስት ሰራተኞችን የሀብት ማስመዝገብ እና ማሳወቅ ሥራም ይሠራል ሲሉ ተናግረዋል።
የሙስና ተግባርን ከመከላከል አንስቶ እስከማጋለጥ የሚደረገው ሂደት ፍሬያማ የሚሆነው የህብረተሰቡ የነቃ ተሳትፎ ሲታከልበት መሆኑን በመገንዘብ ዜጎች ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ሲሉም አሳስበዋል።
አቶ ኮራ ሉኮ እና ተገኝ ጢካ በሶያማ ከተማ እና ሶያማ ዙሪያ ወረዳ የፀረ ሙስና እና ስነምግባር መከታተያ ዳይሬክቶሬት ቡድን መሪ ናቸው። በዓሉን ከማክበር ጎን ለጎን የሀብት ማስመዝገብ ሥራ ትኩረት ተሰጥቶ መመዝገብ እንደሚገባ በነበራቸው ውይይት መግባባታቸውን ተናግረዋል።
ከየሴክተሩ የተወጣጡ የስነምግባር ኦፊሰሮች፣ በዓሉን ሲያከብሩ ህብረተሰቡን በማነቃቃት ስለሙስና አስከፊነት ግንዛቤ እንዲኖረው እና በመከላከሉና በማጋለጡ የድርሻውን ማበርከት እንዲችል መሥራት ይጠበቃል የሚል ግብ እንደተያዘ አብራርተዋል።
ዘጋቢ፦ አብዶ አየለ- ከይርጋጨፌ ቅርንጫፊ

More Stories
የክህሎት ዘርፍ የልማት ሞተር እና የቴክኖሎጂ ሽግግር መሰረትና የስራ ፈጠራ ዋንኛ ምንጭ መሆኑ ተገለፀ
የጎርደና ሴራ አካል የሆነው የኦማኖ ባህላዊ የዳኝነት ስርዓት ለመንግስታዊው የፍትህ ስርዓት ከፍተኛ እገዛ እያደረገ መሆኑ ተገለፀ
የአንታሊያው ኮፕ 31 ጉባኤ የመጨረሻ ቀኑ ላይ ይገኛል