ለአፍሪካ እግር ኳስ ባለውለታው ይድነቃቸው ተሰማ የተዘጋጀው የመታሰቢያ ሐውልት ተመረቀ

ለአፍሪካ እግር ኳስ ባለውለታው ይድነቃቸው ተሰማ የተዘጋጀው የመታሰቢያ ሐውልት ተመረቀ

ለኢትዮጵያ ብሎም ለመላው አፍሪካ እግር ኳስ እድገት የማይተካ አሻራ ያሳረፉት የታላቁ የስፖርት ሰው ክቡር አቶ ይድነቃቸው ተሰማ የመታሰቢያ ሐውልት፣ በአዲስ አበባ በአዲስ መልክ እየተገነባ በሚገኘው ዘመናዊው የአደይ አበባ ስታዲየም ፊት ለፊት በግርማ ሞገስ ቆሟል።

የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ እና የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አበቤ ትናንት ምሽት የክቡር ይድኘቃቸው ተሰማ መታሰቢያ ሀውልትን ጨምሮ በአዲስ አበባ የተገነቡ ሌሎች የልማት ስራዎችን አስመርቀዋል።

ይህ የመታሰቢያ ሐውልት በአፍሪካ እግር ኳስ ታሪክ ውስጥ እጅግ ተጽዕኖ ፈጣሪ ከነበሩት መሪዎች አንዱ ለሆኑት ለይድነቃቸው ተሰማ የተበረከተ ታላቅ ክብርና እውቅና ነው።

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽንን (CAF) በመመስረትና በመምራት፣ እንዲሁም አህጉሪቱ በዓለም አቀፉ የእግር ኳስ መድረክ ተገቢውን ቦታና ውክልና እንድታገኝ በማድረግ ረገድ ያበረከቱት አስተዋጽኦ መቼም ቢሆን የማይረሳ ታሪካዊ ቅርስ ነው።

አዲሱ የአደይ አበባ ስታዲየም የኢትዮጵያን ስፖርት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ታልሞ በመገንባት ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ በመግቢያው ላይ የክቡር አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ሐውልት መቆሙ ለስታዲየሙ ልዩ ታሪካዊ ትርጉምና ድምቀት ሰጥቶታል።

የይድነቃቸው ተሰማ ራዕይ፣ ቁርጠኝነት እና ለእግር ኳስ የነበራቸው ጥልቅ ፍቅር ዛሬም ድረስ ለአዳዲስ ትውልድ የአፍሪካ ተጫዋቾች፣ አሰልጣኞች እና የስፖርት አመራሮች ታላቅ የመነሳሳት ምንጭ ሆኖ ቀጥሏል።

ሐውልቱ ወደ ስታዲየሙ የሚመጡ የስፖርት ቤተሰቦችና ጎብኚዎች የዚህን ታላቅ ኢትዮጵያዊ ባለውለታ ታሪክ እንዲዘክሩና ፈለጋቸውን እንዲከተሉ የሚያበረታታ ሕያው ምስክር ሆኖ ያገለግላል።

ዘጋቢ ፡ ሙሉቀን ባሳ