የውጤት ቀመሩ የጠፋው እግር ኳሳችን
የትናንት እንቅፋቶች ደጋግመው እየመቱን ነው፡፡ በታሪክም ሆነ አሁን እየገጠመን ካለው ችግር መውጣት አልቻልንም፡፡ ዛሬም በውጤት ማጣት እያነከስን ነው፡፡ እግር ኳሳችን አሁንም እንደታመመ ቀጥሏል፡፡
የሚገርመው ኢትዮጵያ ውጤታማ የሆነችበት ስፖርት አትሌቲክሱ ነው፡፡ በአንጻሩ እንደ አሸን መዋዕለ ንዋዩ እየፈሰሰ ያለው እግር ኳሱ ላይ ነው፡፡ ያም ሆኖ ውጤት ላይ ጠብ የሚል ነገር የለም፡፡ ውጤትና ብሔራዊ ቡድኑ የተኳረፉ ይመስል ሆድና ጀርባ ሆነዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድኑ ለአፍሪካም ሆነ ዓለም ዋንጫ የማጣሪያ ውድድሮችን ባደረገ ቁጥር መሳተፍ የማይችልበትን ውጤት ማስመዝገብ እንደተሳነው መስማትም ሆነ ማየት የተለመደ ሆኗል፡፡
ተናንቆም ቢሆን ለአፍሪካ ዋንጫ ቢያልፍ እንኳን በውድድሩ ጥሩ የሚባል አቋም እንኳን ሳያሳይ ከምድቡ ሳያልፍ ይሰናበታል፡፡ ብቻ እግር ኳሱ ዛሬም ከወደቀበት አልተነሳም፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን (ዋሊያዎቹ) በአውሮፓዊያኑ 1957 ነበር በአፍሪካ መድረክ ተሳትፎ ማድረግ የጀመረው፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ለዓለም ዋንጫም ማጣሪያዎችን ቢያደርግም አንድም ጊዜ ውድድሩ ላይ ተሳትፎ አያውቅም፡፡
የአፍሪካ ዋንጫ መስራች ከሆኑት ከቀዳሚዎቹ አንዷ ኢትዮጵያ ነች፡፡ በመጀመሪያዎቹ ተሳትፎዎችም ጥሩ የሚባል ውጤት አስመዝግባለች፡፡ የመጀመሪያውን ጨምሮ በ11 የአፍሪካ ዋንጫ ውድድሮች ላይ ተሳትፋለች፡፡
ከእነዚህም ሁሌም በታሪክ በኩራት የምንናገረው በፈረንጆቹ 1962 የተካሄደውን ራሷ አዘጋጅታ ዋንጫውን ከፍ ያደረገችበትን ነው፡፡ ከ1960ዎቹ በኋላ ግን የብሔራዊ ቡድኑ አቋም እየወረደ ነው የመጣው፡፡
ከአውሮፓዊያኑ 1982 ጀምሮ ደግሞ ለ31 ዓመታት በመድረኩ ላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን መታየት ተሳነው፡፡ በ2013 (እ.አ.አ) ከ31 ዓመታት በኋላ ዳግም ወደ አፍሪካ ዋንጫ ውድድር ቢመለስም ከምድቡ ማለፍ ተስኖት ለመሰናበት ተገዷል፡፡
ከዚህ በኋላ ለመጨረሻ ጊዜ የተሳተፈው የ2021 የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ነበር፡፡ በዚህም ውድድር ከምድቡ ሳያልፍ ቀርቷል፡፡ ብሔራዊ ቡድኑ ከ31 ዓመታት በኋላ ወደ መድረኩ ከተመለሰ በኋላ በተካሄዱ 8 የአፍሪካ ዋንጫ ውድድሮች፣ በ3ቱ ብቻ ነው ተሳታፊ የሆነው፡፡
አሁንም ብርቅዬ የሆነውን የ1962ቱን ድል ብቻ በኩራት ከማንሳት ባለፈ ስለብሔራዊ ቡድኑ የምናነሳው የተለየ ስኬት የለም፡፡ ይልቅስ አቋሙ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ ይገኛል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአሁኑ ወቅት በ2027 በኬኒያ፣ ታንዛኒያ እና ኡጋንዳ አስተናጋጅነት ለሚዘጋጀው 36ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ በምድብ 10 ከሴኔጋል፣ ሞዛምቢክ እና ሱዳን ጋር ተደልድሎ ጨዋታዎችን እያደረገ ይገኛል፡፡
እስካሁን ድረስ በተጫወተባቸው 4 ጨዋታዎች በሶስቱ ተሸንፎ በአንዱ ብቻ አሸንፎ ከሱዳን ጋር እኩል 3 ነጥብ ቢኖረውም በእርስ በእርስ ግንኙነት በመሸነፉ የምድቡ መጨረሻ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡
ቀጣይ የመጨረሻ 2 ጨዋታዎች ሲቀሩት በሜዳው ሱዳንን እንዲሁም ከሜዳው ውጪ ሴኔጋልን ያስተናግዳል፡፡ በዚሁ ምድብ ሴኔጋል 10 ነጥብ ሰብስባ አስቀድማ ማለፏን አረጋግጣለች፡፡ ሞዛምቢክ በበኩሏ 7 ነጥብ ሰብስባ 2ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሁለተኛ ደረጃ የተቀመጠችውን ሞዛምቢክ በልጦ በሁለተኝነት ከምድቡ ለማለፍ በቀጣይ ሱዳንን እና ሴኔጋልን ሲገጥም ማሸነፍ፣ ጎን ለጎን የሞዛምቢክን መሸነፍ የግድ ይጠብቃል፡፡ ከሱዳንም ጋር ቢሆን ተመሳሳይ ፉክክር ይጠብቀዋል፡፡ ይህ ደግሞ ከፊቱ ከባድ ተራራ የመግፋት ያህል ፈተና መጋረጡን አመላካች ነው፡፡
ለማንኛውም የብሔራዊ ቡድናችን የቁልቁለት ጉዞ አሁንም ቀጥሏል፡፡ አሰልጣኞች በውጤት ማጣት ምክንያት በየጊዜው ቢቀያየሩም የሜዳ ውስጥ ስኬት የውሃ ሽታ ሆኖ ቀርቷል፡፡
በዓመት በብዙ መቶ ሚሊየኖች፣ እንደ አንዳንዶች መረጃ ደግሞ ከቢሊየን በላይ ብሮች ፈሰስ የሚደረግበት እግር ኳሱ ያለ ለውጥ ከነእንቆቅልሹ መቀጠሉ ለስፖርቱ ቤተሰብ አሳዛኝ ክስተት ነው፡፡
ኢትዮጵያ ለብዙ ጊዜያት ስትታማበት የቆየችውን ብቁ ዘመናዊ ስቴዲየም የባህር ዳርን ገንብታ ለውድድር ክፍት በማድረግ ተቺዎቿን ለጊዜውም ቢሆን ዝም ብታሰኝም የብሔራዊ ቡድኑ ውጤታማ አለመሆን ሌላ ራስ ምታት ሆኖባታል፡፡
የዚህ አሳሳቢው ጉዳይ ስቴዲየሙን ባላት የገንዘብ አቅም እንደገነባችው ወደ ውጤት መምጣቱ ቀላል አለመሆኑ ነው፡፡ ይኸው ለበርካታ አስርት ዓመታት ታሪክ ራሱን እየደገመ ቀጥሏል፡፡
የደጋፊው ወኔና የማያቋርጥ ድጋፍ ከብሔራዊ ቡድኑ ተደጋጋሚ የውጤት ቀውስ ጋር ሊጣጣም አልቻለም፡፡ አሁንም እግር ኳሱ የሚታደገውን አካል ይፈልጋል፡፡ በእግር ኳሱ ውስጥ ተሳትፎ የሚያደርጉ ተጫዋቾች፣ አሰልጣኞች፣ የቡድንና የክለብ አመራሮች፣ ፌደሬሽኑ፣ ብቻ የሚመለከተው አካል ሁሉ ቁጭ ብሎ በጠረጴዛ ዙሪያ መምጣት ስላለበት ለውጥ ከልባቸው መምከር ይኖርባቸዋል፡፡
ለውጤት ቀውሱ አሰልጣኞች፣ ተጫዋቾች፣ የአጨዋወት ዘይቤ፣ የቴክኒክና የታክቲክ ጉድለት፣ የእግር ኳሱ አወቃቀር፣ የገንዘብና የሥልጠና እጥረት፣ ፌደሬሽኑ፣ ሌሎች አካላት ወይስ ምክንያቱ ማንና ምንድነው? የሚለውንም ለመለየት በጋራ በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጦ በሰከነ መንፈስ መፈተሽና ችግሩን ለይቶ ለውጤት መስራት የግድ የሚልበት ጊዜ ላይ እንገኛለን፡፡
ለዚህ ግን የሁሉም አካላት ቀናነትና ቁርጠኝነት ያስፈልጋል፡፡ የታመመውን እግር ኳሳችንን በጊዜ እናክመው!! ሰላም!!
ዘጋቢ፡- ኢያሱ ታዴዎስ

More Stories
ኢትዮጵያ ወገቧን ጠበቅ አድርጋ ልታሰናዳ የተዘጋጀችው ኮፕ 32 ጉባኤ
21ኛው የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓልን ለማክበር አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መደረጉን የጌዴኦ ዞን ምክር ቤት አስታወቀ
የሆሳዕና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ከኢትዮ-ቴሌኮም ጋር በመተባበር የትምህርት አስተዳደር ሥርዓትን በይፋ አስጀመረ