ችግሮች በመቋቋም በበጀት ዓመቱ የተሻለ አፈፃጸም መመዝገቡን በደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት የጂንካ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አስታወቀ

ችግሮች በመቋቋም በበጀት ዓመቱ የተሻለ አፈፃጸም መመዝገቡን በደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት የጂንካ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አስታወቀ

ሀዋሳ፡ ሐምሌ 15/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) ችግሮች በመቋቋም በበጀት ዓመቱ የተሻለ አፈፃጸም መመዝገቡን በደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት የጂንካ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ዳኜ ጥላሁን ገለጹ፡፡

ቅርንጫፉ ጽህፈት ቤቱ ዓመታዊ እቅድ አፈጻጸም ግምገማና የቀጣይ አመት ማስፈጸሚያ እቅድ ዙሪያ በጂንካ ከተማ የውይይት መድረክ አካሂዷል።

በውይይት መድረኩ በሁሉም የሚዲያ አማራጮች በሬዲዮና ቴሌቪዥን እንዲሁም በማህበራዊ ሚዲያ አማራጮች በሽፋን ደረጃ ይሳኩ ዘንድ በበጀት ዓመቱ በተደረጉ ጥረቶች የተመዘገቡ ውጤቶች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

በዚህም በሽፋን ደረጃ ስኬታማ አፈጻጸም ማስመዝገብ የተቻለ ሲሆን ለሁሉም አካባቢዎች በፍትሃዊነት ሽፋን በመስጠት ረገድ የታዩ ውስንነቶችን ማሻሻልና ጥንካሬዎችን ማስፋት እንዲሁም ጥራትን የማሳደግ ስራዎች ትኩረት የሚሹ ስለመሆናቸው ተመላክቷል።

የተቋሙ ሰራኞችም ለአፈጻጸም ሂደት ተግዳሮት እየሆኑ ያሉ የሚዲያ ቴክኖሎጂ ቁሳቁሶች፤ የስራ ስምሪትና የበጀት ውስንነቶች በዝርዝር አንስተው ለቀጣይ አመት ይታረሙ ዘንድ ጠይቀዋል።

የተቋሙ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ዳኜ ጥላሁን በየስራ ክፍሎቹ ያሉ ችግሮች በመቋቋም እቅዶቹን ለመፈጸም የተደረጉ ጥረቶችን አድንቀው በስኬት የተመዘገቡ ድሎች የጋራ ጥረት ውጤቶች በመሆናቸው ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ የዉስጥ ገቢን ለማሳደግ በተከናወኑ ዘርፈብዙ ተግባራት ከዕቅድ በላይ ማሳካት መቻሉም ተገልጿል።

በዋናነትም የሚዲያ ፍትሃዊ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የስርጭት ሽፋን የመቋረጥ ችግሩን ለመቅረፍ ዘርፈ ብዙ ጥረቶች እየተደረጉ መሆናቸውን ጠቅሰው ከቴክኖሎጂ ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመፍታም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር በትኩረት እንደሚሰራም ነው ያረጋገጡት።

በመድረኩ የ2019 ዓ.ም ጠቋሚ ዕቅድ ቀርቦ ውይይት ተካሂዷል።

ወጋቢ፡ ወንድሜነህ አድማሱ – ከጂንካ ጣቢያችን