የሴቶችን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነትንና ተሳትፎን ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ
ሀዋሳ፡ ሐምሌ 15/2018(ደሬቴድ) የሴቶችን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነትንና ተሳትፎን ለማረጋገጥ በትኩረት እየሰራ መሆኑን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የወልቂጤ ክላስተር የመንግስት ሰራተኛ ሴቶች ማህበር ገለፀ ።
ማህበሩ በ2018 በጀት አመት አፈፃፀምና በክረምት ወራት በበጎ ፍቃድ አገልግሎት ስራዎችና በቀጣይ አቅጣጫዎች ዙሪያ ከአባላቱ ጋር የውይይት መድረክና የችግኝ ተከላ መረሃ ግብር በወልቂጤ ከተማ አካሂዷል፡፡
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሴቶች ማህበር ስራ አስፈፃሚና የወልቂጤ ክላስተር አባል ወ/ሮ ፈቲያ ጀማል ሴቶች ማህበራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ በተናጥል ከመንቀሳቀስ በተለያዩ አደረጃጀቶች መደራጀት እንዳለባቸው አስረድተዋል።
ይህም በየደረጃው ሴቶችን ለማብቃትና ተሳትፎቸውን ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው አስታውቀዋል፡፡
በክልሉ የወልቂጤ ክላስተር የመንግስት ሰራተኛ ሴቶች ማህበር ሰብሳቢ ወ/ት ሀስና ኸሊል በበኩላቸው ማህበሩ ከተመሰረተ አጭር ጊዜ ቢሆንም ውጤታማ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።
ማህበሩ በ2018 በጀት አመት የነበሩ ጠንካራ ጎኖችና ውስንነቶችን በመለየት በ2019 በጀት አመት የተሻለ ስራ ለመስራት ግብ መያዙን የተናገሩት ሰብሳቢዋ ማህበሩ 831 አባላት እንዳሉትና በቀጣይም ቁጥሩን ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል ።
የማህበሩ ፀሀፊና ስራ አስፈፃሚ ወ/ሮ ገነት ታደሰ እንደገለፁት በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች ሴቶች በማህበር ተደራጅተው ማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነታቸውን እያሳደጉ ይገኛሉ።
በመሆኑም በክላስተሩ የሚገኙ የመንግስት ሴት ሰራተኞችን ከማደራጀትና የማህበሩ አባላት ቁጥር ከማድረግ በሻገር ኢኮኖሚያዊ አቅማቸውን በማሳደግ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ እየተሰራ ይገኛል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የመረሃ ግብሩ ተሳታፊ የማህበሩ አባላት በሰጡት አስተያየት በማህበር መደራጀታቸው ያላቸውን እውቀትና ክህሎት በመጠቀም በየደረጃው በሚከናወኑ ተግባራት ያላቸውን ተሳትፎና ተሰሚነት ለማሳደግ ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው ገልፀዋል፡፡
በተለይም በተለያዩ ሀገራዊ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላና በሌሎችም ወቅታዊ ጉዳዮች በንቃት በመሳተፍ ላይ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የማህበሩ የ2018 በጀት አመት የስራ አፈፃፀምና በቀጣይ በክረምት ወራት በበጎ ፍቃድ አገልግሎት ስራዎችና አቅጣጫዎች ዙሪያ ግምገማ ነክ ውይይት የተደረገ ሲሆን የማህበሩ አመራሮችና አባላት በክልሉ በቀቤና ልዩ ወረዳ ዘቢሞላ ቀበሌ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ አካሂደዋል ።
ዘጋቢ፡ እቴነሽ ቴሬቦ – ከወልቂጤ ጣቢያችን

More Stories
የባስኬቶ ዞን ሽግግር ምክር ቤት 4ኛ ዙር 10ኛ ዓመት የስራ ዘመን 3ኛ አስቸኳይ ጉባኤ እያካሄደ ነው
ችግሮች በመቋቋም በበጀት ዓመቱ የተሻለ አፈፃጸም መመዝገቡን በደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት የጂንካ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አስታወቀ
መንግስት ለትምህርቱ ዘርፍ የሰጠውን ትኩረት ሁሉም ያለ ስስት ሊደግፍ እንደሚገባ ተገለጸ