መንግስት ለትምህርቱ ዘርፍ የሰጠውን ትኩረት ሁሉም ያለ ስስት ሊደግፍ እንደሚገባ ተገለጸ
ሀዋሳ፡ ሐምሌ 15/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) መንግስት ለትምህርቱ ዘርፍ የሰጠውን ትኩረት ሁሉም ያለ ስስት ሊደግፍ እንደሚገባ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የዲላ ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ ገለጸ፡፡
መምሪያው “ለትምህርት ያለ ስስት” በሚል መሪ ቃል የትምህርት ንቅናቄ መድረክ በዲላ ከተማ አካሂዷል።
ትምህርት ቤቶች ለመማር ማስተማር ሥራ ምቹ፣ ለተማሪዎች ሳቢ እና ማራኪ በማድረግ የትምህት ውጤታማነት ለማሻሻል በተሰራው ሥራ አመርቂ ውጤት መመዝገቡን የዲላ ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ዮሴፍ ሆርዶፋ በመክፈቻ ንግግራቸው አስረድተዋል።
የትምህርት ባለድርሻዎች፣ የንግዱ ማህበረሰብና ባለሀብቶች፣ የሀይማኖትና የባህል አባቶች እንዲሁም ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በተካሄደው ንቅናቄ በከተማ አስተዳዱሩ ውስጥ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች የቅድመ ዝግጅት ምዕራፍ ሥራዎች በስፋት ተዳሰዋል።
መድረኩን በንግግር የከፈቱት የዲላ ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ዮሴፍ ሆርዶፋ፥ በተጠናቀቀው የትምህርት ዘመን የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻልና የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሳደግ በተሰሩ ሥራዎች አበረታች ውጤት መመዝገቡን አስረድተዋል።
በዚህም የትምህርት ቤቶች ደረጃ በእጅጉ እየተሻሻለ መምጣቱን የጠቆሙት ኃላፊው፥ የተማሪዎች ውጤትም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን አስታውቀዋል።
በመድረኩ የዲላ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የሥራና ክህሎት መምሪያ ኃላፊ አቶ ታሪኩ በየነ፥ መንግስት የትምህርት ጥራትና ተደራሽነት ላይ ሲታዩ የነበሩ ማነቆዎችን ለመፍታት የወሰደው እርምጃ ውጤት እያስመዘገበ መሆኑን ገልጸዋል።
በከተማ አስተዳደር ደረጃ የትምህርት ቤቶችን የመሠረተ ልማት ችግር በመፍታት፣ የዲጂታል አሰራሮችን በማጠናከርና የትምህርት መስጫ ግብዓቶችን በማሟላት ብቁና ተወዳዳሪ ዜጋን ለማፍራት እየተሰራ መሆኑን አቶ ታሪኩ አስታውቀዋል።
የትምህርት ሥራ የሁሉንም የነቃ ተሳትፎ የሚጠይቅ በመሆኑ ከትምህርቱ አመራር ጎን በመሆን ሁሉም ዘርፉን ያለ ስስት እንዲደግፍ ኃላፊው ጥሪ አቅርበዋል ።
ዘጋቢ : ሳሙኤል በቀለ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን
መንግስት ለትምህርቱ ዘርፍ የሰጠውን ትኩረት ሁሉም ያለ ስስት ሊደግፍ እንደሚገባ ተገለጸ

More Stories
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ብሔረሰቦች ምክር ቤት 6ኛ ዙር 5ኛ ዓመት 4ኛ መደበኛ ጉባኤውን በኮንሶ ዞን ካራት ከተማ እያካሄደ ይገኛል
በ2018 ዓ.ም የ8ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከወሰዱ ተማሪዎች 97.48% የማለፊያ ውጤት ማስመዝገብ መቻላቸውን የከምባታ ዞን ትምህርት መምሪያ አስታወቀ
የዜጎችን ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግና የአገርን እድገት ለማስቀጠል ግብር በወቅቱና በታማኝነት መክፍል ያለው ድርሻ የጎላ መሆኑ ተገለጸ