በ2018 ዓ.ም የ8ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከወሰዱ ተማሪዎች 97.48% የማለፊያ ውጤት ማስመዝገብ መቻላቸውን የከምባታ ዞን ትምህርት መምሪያ አስታወቀ

በ2018 ዓ.ም የ8ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከወሰዱ ተማሪዎች 97.48% የማለፊያ ውጤት ማስመዝገብ መቻላቸውን የከምባታ ዞን ትምህርት መምሪያ አስታወቀ

የከምባታ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ዳዊት አሹሮ እንደገለፁት በዓመቱ በአጠቃላይ በስምንተኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና የወሰዱ 11ሺ 504 ተማሪዎች መሆናቸውን አመላተው፥ ከእነዚህም 11 ሺ 214 ተማሪዎች የማለፊያ ነጥብና ከዚያ በላይ በማስመዝገብ ወደ ቀጣይ ክፍል መሸጋገር መቻላቸውን ገልፀዋል።

የዘንድሮ የ8ኛ ክፍል ውጤት ካለፉ አመታት ተመሳሳይ የተማሪዎች ውጤት ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ ለውጥ ማሳየቱን የተናገሩት ኃላፊው፥ የተማሪዎች ውጤት ዕድገት የሚያሳየው መንግስት ለትምህር ጥራት የሰጠውን ልዩ ትኩራት ነው ብለዋል።

ከዚህ ቀደም በ8ኛ ክፍል አንድም ተማሪ ማለፍያ ውጤት ሳያስመዘግቡ የቀሩ ትምህርት ቤቶች እንደነበሩ ያስተወሱት አቶ ዳዊት፥ በዘንድሮ 2018 ዓ.ም በትምህርት ቤቶችና በትምህርት ዓይነቶች ጉልህ ለውጥ መመዝገቡን ገልፀው 2017 ዓ.ም አንድ ተማሪ እንኳ ያላሳለፉ ትምህርት ቤቶች ጭምር የማለፍያ ውጤት ማስመዝገብ መቻላቸውን አስረድተዋል ።

በ2018 ዓ ም በ8 ኛ ክፍል ካስፈተኑ 196 ትምህርት ቤቶች የማለፍያ ውጤት ያላስመዘገበ ትምህርት ቤት በዞኑ እንደሌለ ገልፀዋል ።

በአብዛኞቹ ትምህርት አይነቶች ከፍተኛ የውጤት መሻሻል መታየቱን የተናገሩት ኃላፊዉ በተላይም በሒሳብ፣ እንግሊዘኛ እና በዜግነት የትምህርት ዓይነቶች ከፍተኛ ውጤት መኖሩን አስረድተው በአንፃሩ የከምባቲኛ ትምህርት ውጤት ላይ የውጤት መውረድ ተስተውሏል ብለዋል።

ኩረጃን ለመከላከል ሥርዓት ተዘርግቶ ፈተናው በክላስተር ማዕከላት በክልላዊ ሱፐርቫይዘሮች ክትትል መደረጉ ውጤት እንደነበረው አንስተዋል።

ውጤቱ በተከታታይ ለትምህርት ጥራት በተሰሩ ስራዎች መሆኑን ተናግረው የማጠናከሪያ ትምህርት፣ ሞዴል ፈተናዎች እና የተማሪዎች ስነ ልቦና እንዲዘጋጅ የተሰሩ ስራዎች ለተመዘገበው ውጤት ድርሻቸው ከፍ ያለ ነው ሲሉም ገልፀዋል ።

ዘጋቢ: አለማየሁ ማተቦ – ከሆሳዕና ጣቢያችን