የዜጎችን ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግና የአገርን እድገት ለማስቀጠል ግብር በወቅቱና በታማኝነት መክፍል ያለው ድርሻ የጎላ መሆኑ ተገለጸ

የዜጎችን ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግና የአገርን እድገት ለማስቀጠል ግብር በወቅቱና በታማኝነት መክፍል ያለው ድርሻ የጎላ መሆኑ ተገለጸ

‌‎ሀዋሳ፡ ሐምሌ 15/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የዜጎችን ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግና የአገርን እድገት ለማስቀጠል ግብር በወቅቱና በታማኝነት መክፍል ያለው ድርሻ የጎላ መሆኑን የኮንታ ዞን ጪዳ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ፡፡

የኮንታ ዞን ጪዳ ከተማ አስተዳደር የ2019 በጀት ዓመት የደረጃ ‘ለ’ እና ‘ሀ’ የግብር ማስጀመሪያ ንቅናቄ መድረክ ተካሂዷል።

የጪዳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ዓለሙ ኮቾ በየጊዜው እያደገ የመጣውን የህዝብ ሁለንተናዊ ፍላጎትን ለማሟላት የገቢ አቅምን ማሳደግ እንዳለበት በመጠቆም ለከተማችን ዕድገትና ለውጥ የግብር ከፋዮች ሚና ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

‎አያይዘውም አቶ ዓለሙ ግብር ከፋዮች ያለ ግዴታ ወደውና ፈቅደው ግብር በመክፈል የዜግነት ግዴታቸውን መወጣት እንዳለባቸው ጠቁመው፥ ግብር ከፋዮችን በቅንነት፣ በታማኝነት እና በተቀላጠፈ መንገድ ለማስተናገድ እየተሰራ በመሆኑ፥ ግብርን በታማኝነት መክፈል የሀገር ፍቅር ማሳያ ነው ብለዋል።

‎የጪዳ ከተማ አስ/ር ኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪ አቶ መስፍን ማሞ በበኩላቸው፥ የከተማችን ዕድገት እንዲፋጠን የነጋዴው ማህበረሰብ አስተዋዕጾ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

የዘንድሮው የግብር ዘመን አከፋፈል በዘመናዊ መንገድ መሆኑ ጊዜና ጉልበታቸዉን እንደቆጠበላቸዉ ጠቁመዉ ቀጣይም ይህ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ተናግረዋል።

‎ባለፈው ዓመት በግብር ከፋዮች ዘንድ ጥሩ መነቃቃት እንደነበር ጠቅሰው በዘንድሮው ዓመትም ግብር ከፋዮች ቁርጠኞች እንዲሆኑ አሳስበዋል።

‎በግብር አሰባሰብ ዙሪያ እና በአዲሱ የግብር ማሻሻያ አዋጅ ዙሪያ የከተማ አስተዳደሩ ገቢዎች ዩኒት አቶ ታምራት ደሳለኝ ሰነድ አቅርበው ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል።

‎ለውጥን ለማስቀጠልና ልማትን ለማፋጠን በወቅቱ ግብርን በመክፈል የዜግነት ግዴታችንን እንወጣለን ሲሉ ተሳታፊዎች ገልጸዋል።

ዘጋቢ፡ ደረጀ ተፈራ – ከዋካ ጣቢያችን