የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ከነበረበት የብልሹ አሰራር እና የቴክኖሎጂ ኋላ ቀርነት ወጥቶ የሀገርን ገጽታ በሚመጥን መልኩ ስር ነቀል ሪፎርም እያከናወነ መሆኑ ተገለፀ
በሚዛን አማን ከተማ አገልግሎት እየሰጠ ያለው የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት በተሟላ ሁኔታ ወደ ስራ መግባቱ ከእንግልት ታድጎናል ሲሉ ተገልጋዮች ተናግረዋል።
በሚዛን አማን ከተማ የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት በተሟላ ሁኔታ ወደ ስራ መግባት ቀደም ሲል ሲገጥማቸው ከነበረ እንግልት እንደታደጋቸው ተገልጋዮቹ ገልጸዋል።
በኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት የሚዛን አማን ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ከተከፈተበት ጊዜ ጀምሮ የአዲስ ፓስፖርት ማውጣት፣ የነባር ፓስፖርት ዕድሳት፣ የእርማትና ሌሎችንም ጨምሮ የተሟላ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።
መንግሥት ለሕዝቡ ቅርብ የሆነ የአገልግሎት ሥርዓት መዘርጋቱ፣ ከዚህ ቀደም አገልግሎቱን ለማግኘት ያጋጥማቸው ከነበረው የጊዜና የገንዘብ ብክነት እንደታደጋቸው የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ተናግረዋል።
አስተያየታቸውን ከሰጡን ተገልጋዮች መካከል አቶ ቀኒቶ ማቲዮስ፣ ቄስ ቢኒያም ኤርሞ፣ ወጣት መሰረት አበራ እና ወጣት ኢክራም አደራ፤ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቱ በሚዛን አማን በመከፈቱ ምክንያት ወደ ጅማና አዲስ አበባ በመጓዝ ያወጡት ከነበረው የትራንስፖርት፣ የአልጋና ተያያዥ ወጪዎች መዳናቸውን ገልፀው ከምንም በላይ የጊዜ ብክነትንና የረጅም ወራት ቀጠሮ እንግልትን በማስቀረቱ እንዲሁም ከዚህ ቀደም ረዘም ያለ ጊዜን ይወስድ የነበረውን አገልግሎት አሁን ላይ በአጭር ጊዜ ውስጥ አጠናቀው ፓስፖርት ማግኘታቸው እንዳስደሰታቸው ገልፀዋል።
አሰራሩ ቀልጣፋና በቴክኖሎጂ የተደገፈ በመሆኑ ከዚህ ቀደም ረጅም ጊዜ ይወስድ የነበረው አገልግሎት በአጭር ጊዜ ስለሚጠናቀቅ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረው፤ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
በኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት የሚዛን አማን ኢሚግሬሽን ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጀማል ደስታው፤ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቱ ከተከፈተበት ጊዜ ጀምሮ አዲስ የፓስፖርት ማውጣት፣ የነባር ፓስፖርት ዕድሳት እና እርማትን ጨምሮ የተሟላ አገልግሎት እየሰጡ በመሆኑ ህብረተሰቡን ከእንግልት መታደግ መቻሉን ገልፀዋል።
ዜጎች ባሉበት አካባቢ ሆነው በቅርበት አገልግሎት እንዲያገኙ በማለም የተቋቋመው የሚዛን አማን ቅርንጫፍ መደበኛ ብቻ ሳይሆን አስቸኳይ አገልግሎቶችን እየሰጠ እንደሚገኝም ኃላፊው ጠቁመዋል።
በዚህም በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልልና በአቅራቢያው ለሚገኙ ዜጎች ምቹ ሁኔታ መፈጠሩንና በነባር የአገልግሎት ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ላይ ይታይ የነበረውን የወረፋ መጨናነቅ መቀነስ መቻሉን ተናግረዋል።
ዘጋቢ፡ ተመስገን ዳጉሳ – ከሚዛን ጣቢያችን

More Stories
ኢትዮጵያ እየመከረች ነው!
ሀገራዊ ምክክሩ ኢትዮጵያ በዘመናት የመንግስት ታሪኳ ውስጥ የሚፈትናትን የሠላም ማጣት ሊቀርፍላት ይችላል ሲሉ በኣሪ ዞን የጂንካ ከተማ ነዋሪዎች ገለፁ
በአርባምንጭ አካል ጉዳተኞች ተሃድሶ ማዕከል እየተሰጠ ያለው አገልግሎት ይበልጥ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ተገለጸ