በአርባምንጭ አካል ጉዳተኞች ተሃድሶ ማዕከል እየተሰጠ ያለው አገልግሎት ይበልጥ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ሐምሌ 14/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) በአርባምንጭ አካል ጉዳተኞች ተሃድሶ ማዕከል እየተሰጠ ያለው አገልግሎት ይበልጥ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ተገለጋዮቹ ገለጹ፡፡

በማዕከሉ የሚስተዋሉ የግብዓት እና የሰው ሐይል ችግሮች መቀረፍ እንዳለባቸውም ተጠይቋል።

‎ማዕከሉ የቁሳቁስ ማምረቻ ማዕከል ከመገንባቱም በተጨማሪ በዘርፉ እየተስተዋሉ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ አስታውቋል።

‎በአርባምንጭ አካል ጉዳተኞች ተሃድሶ ማዕከል ከወላይታ ሶደ ከተማ የተገኘው ወጣት ታምሩ ጌታቸው በሁለቱም እግሩ ላይ የአካል ጉዳት የደረሰ ሲሆን፤ በተሰራለት አርቴፊሻል ድጋፍ በጥሩ ሁኔታ እየተቀሳቀሰ መሆኑን ተናግሯል።

‎ሌላኛዋ ከተማ ነዋሪ አካል ጉዳተኛ ወ/ሮ አሚናት መሐመድ፤ በማዕከሉ ለ20 ዓመታት በተደረገላቸው አገልግሎት ተጠቃሚ በመሆናቸው መደሰታቸውን ገልፀው፤ መቀረፍ ያለባቸው ጉዳዮች እንዳሉም ጠቁመዋል።

‎በማዕከሉ የፊዚዮትራፒ ክፍል አስተባባሪ አቶ ደኢሶ ጎንሳሞ እና የሰው ሰራሽ አካልና የአካል ድጋፍ ምርት ክፍል ስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ወንዱ ዓለማየሁ በተፈጥሮና በተለያዩ ምክያቶች የአካል ጉዳት ለደረሰባቸው ዘርፈ ብዙ አገልግሎት እየተሰጣቸው እንደሆነ ገልፀው፤ ለስራቸው እንቅፋት የሆኑ ጉዳዮች መኖራቸውን አንስተዋል።

‎የአርባምንጭ አካል ጉዳተኞች ተሃድሶ ማዕከል ሥራ አስኪያጅ አቶ ኢዮብ አንዳለ በበኩላቸው፤ በማዕከሉ አራት ዋና ዋና ዘርፎች ለአካል ጉዳተኞች አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን አስረድተዋል።

‎በሀገሪቱ በአራት ክልሎች ማዕከሉ ተደራሽ አድርጎ አገልግሎት እየሰጠ ነው ያሉት ሥራ አስኪያጁ፤ ይበልጥ ስራውን ለማሳለጥ የቁሳቁስ ማምረቻ ማዕከል ከመገንባቱም ባሻገር በዘርፉ እየተስተዋሉ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም አመላክተዋል።

‎ዘጋቢ ፡ እንጃ ገልሲሞ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን