ሀገር አቀፍ የተቀናጀ የጤና ዘመቻ ማስጀመሪያ መርሀ ግብር በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጋሞ ዞን ላንቴ ቀበሌ እየተካሔደ ነው



በዘመቻው ተላላፊ እና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ልየታ እና የሕክምና አገልግሎት ይሰጣል።

በዘመቻው የፌዴራል ጤና ሚኒስቴር የፕሮግራም ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ አቶ ሌሊሳ አማኑኤልን ጨምሮ የክልል የዞንና አጋር ድርጅቶች እየተሳተፉበት ይገኛል።

ከሐምሌ 13 እስከ 24 /2018 ዓ.ም እየተካሔደ ባለው በዚሁ ዘመቻ በአገሪቱ ባሉ 08 ክልሎች በ401 ወረዳዎች ተደራሽ የሚያደርግ ሲሆን ከ41 ሚሊዮን 665ሺህ በላይ የማህረሰብ ክፍሎች የዘመቻ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ የፌዴራል ጤና ሚኒስቴር ዴኤታ ከፍተኛ አማካሪ አቶ ሌሊሳ አማኑኤል ገልጸዋል፡፡

አክለውም ባለፉት ሁለት ዓመታት የጤናውን ዘርፍ ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር በተሠራው ሥራ ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልጸው በየጊዜው የሚሰጡ የተቀናጀ የዘመቻ ሥራ በአንድ ማዕከል ወጪ እና ጊዜ ቆጣቢ በሆነ መንገድ የሚሰጥ በመሆኑ ውጤታማ ተግባራት ይሠራሉ ብለዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ሀላፊ እና የጤና ፕሮግራሞች ዘርፍ ሀላፊ አቶ መና መኩሪያ በዘመቻው የወባ በሽታ፣የዓይን ሕክምና ልየታ፣ የማህጸን ጫፍ ካንሰር ልየታ፣ የቲቢ፣ የዝሆኔ እና ኦንኮርሰያስስ በሽታዎችን በመለየት እና ሕክምና አገልግሎት ለመስጠት ያለመ በመሆኑ የጤና ተደራሽነቱን ለማስፋት ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል።

ለዘመቻው መሳካት ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ አቶ መና አሳስበዋል።

የጋሞ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ እና የሥራና ክህሎት መምሪያ ሀላፊ አቶ ሀኪሜ አየለ እንዳሉት ጤናው የተጠበቀ ማህበረሰብ የልማት ትልሞችን ለማሳካት ብቁ በመሆኑ መንግሥት በበሽታ መከላከሉ እና አክሞ ማዳን ላይ በትኩረት እየሠራ ነው።

በዞኑ የጤና አገልግሎት ውጤታማ ለማድረግ በመንግሥት እና በህብረተሰብ ተሳትፎ የተሠሩ ተግባራት አመርቂ መሆናቸውን አቶ ሀኪሜ ተናግረዋል።

ፕሮግራሙ በኢፌዴሪ ጤና ሚኒስቴር ፣ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ፣ ካርተር ሰንተር ኢትዮጵያ እና የአለም ጤና ድርጀት ጋር በመተባበር የተዘጋጀ መሆኑም ተመላክቷል።

የተቀናጀ የበሽታ ልየታ እና ህክምና ‘TELECOM+’ በዞኑ በአርባ ምንጭ ዙሪያ በጋጮ ባባ እና ቦረዳ ወረዳዎች እስከ ሐምሌ 24 ድረስ መሰጠት መጀመሩም ታውቋል።

ዘጋቢ: ወ/ገብርኤል ላቀው – ከአርባ ምንጭ ጣቢያችን