የወባ በሽታን ጨምሮ 7 ያህል የሐሩራማ አካባቢ በሽታዎች ለመከላከል የሚያስችል የመድሃኒት እደላና የተቀናጀ የጤና ዘመቻ ስራ በይፋ መጀመሩ ተገለጸ

የወባ በሽታን ጨምሮ 7 ያህል የሐሩራማ አካባቢ በሽታዎች ለመከላከል የሚያስችል የመድሃኒት እደላና የተቀናጀ የጤና ዘመቻ ስራ በይፋ መጀመሩ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ሐምሌ13/2018 ዓ.ም(ደሬቴድ) የወባ በሽታን ጨምሮ 7 ያህል የሐሩራማ አካባቢ በሽታዎች ለመከላከል የሚያስችል የመድሃኒት እደላና የተቀናጀ የጤና ዘመቻ ስራ በይፋ ማስጀመሩን የአሪ ዞን ጤና መምሪያ አስታወቀ።


በዓለም ጤና ድርጅትና በካርተር ሴንተር ኢትዮጵያ ድጋፍ የሚካሄደው ዘመቻ የማስጀመሪያ መርሃ ግብር በዞኑ ደቡብ ኣሪ ወረዳ አይካመር ቀበሌ በይፋ ተካሂዷል።

በዚሁ መርሀ ግብር ወቅት ንግግር ያደረጉት የዞኑ ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ በድሉ ባጊማሶ ወባን ጨምሮ ከ7 በላይ የማህበረሰብ የጤና ችግሮችን ለመፍታት ያለመው መርሀ ግብር በተለያዩ የዞኑ አካባቢዎች የሚካሄድ መሆኑን አስታውቀዋል።

ዘመቻው በዋናነት የሀሩራማ አካባቢ በሽታዎችን ጨምሮ፤ የወባ በሽታ፤ የማህጸን ጫፍ ካንሰር፤ የቲቪ በሽታ ልዬታና ሌሎች ተዛማጅ የጤና ችግሮችን መከላከል ላይ አትኩሮ የመድሃኒት እደላም የሚካሄድበት መሆኑንም አስረድተዋል።

ለዘመቻው ስኬት ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል።

የደቡብ ኣሪ ወረዳ ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ትንሹ ተክሌ በበኩላቸው ሀገርን ለማበልጸግ ጤናማ ዜጋን ማፍራት ወሳኝ በመሆኑ የህብረተሰብ ጤና ችግሮችን ለመፍታት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ወባን ጨምሮ አሳሳቢ የሆኑ የጤና ችግሮችን ለመፍታት በደቡብ አሪ ወረዳ ከ18 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ ተደርጎ እየተሰራ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

በክልሉ የተቀናጀ በሽታን የመከላከል ዘመቻና የመድሃኒት እደላ በአርባምንጭ ከተማ በይፋ መጀመሩን ጠቅሰው 10 ዞኖችን ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ እንደሚገኝ የገለጹት ደግሞ በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የክልሉ ጤና ቢሮ የወባ መከላከልና መቆጣጠር ፎካል የሆኑት አቶ አይቼው ሙላቱ ናቸው።

በሚካሄደው የመድሃኒት እደላና የተቀናጀ የጤና ዘመቻ በክልሉ በአጠቃላይ ከ 938 ሺህ በላይ ዜጎችን ተደራሽ ለማድረግ መታቀዱን ጠቅሰው በኣሪ ዞን በሚገኙ 5 ወረዳዎች ከ336 ሺህ በላይ ዜጎች ተደራሽ ይደረጉበታል ብለዋል።

በተጓዳኝም ወባን የመከላከል ዘመቻና ሌሎች የሐሩራማ አካባቢ የጤና ችግሮች የልዬታና የመድሀኒት እደላ ስራዎች በተቀናጀ መልኩ ይከናወናሉ ብለዋል።

ዘመቻው በስኬት ይካሄድ ዘንድም አርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ በጥናት የታገዘ ሳይንራዊ እገዛ እያደረገ የሚገኝ ስለመሆኑም ለመረዳት ተችሏል።

ዘጋቢ ፡ ወንድሜነህ አድማሱ – ከጂንካ  ጣቢያችን