በ2018/19 መኸር እርሻ ከ30 ሺህ 9 መቶ በላይ ሄክታር መሬት በተለያዩ አዝርዕት ለመሸፈን መታቀዱን የሀላባ ዞን ግብርና መምሪያ አስታወቀ

በ2018/19 መኸር እርሻ ከ30 ሺህ 9 መቶ በላይ ሄክታር መሬት በተለያዩ አዝርዕት ለመሸፈን መታቀዱን የሀላባ ዞን ግብርና መምሪያ አስታወቀ

የዘር እና የማዳበሪያ አቅርቦት በሁሉም አካባቢዎች በወቅቱ ተደራሽ የማድረግ ሥራ በትኩረት እየተከናወነ ስለመሆኑም ተጠቁሟል::

የሀላባ ዞን ግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊና የእርሻ ዘርፍ ኃላፊ አቶ አብዱልረህማን ኡስማን እንደገለፁት፤ በዘንድሮው ለመኸር እርሻ በተዘጋጀው መሬት የበርበሬ፣ የጤፍ፣ የስንዴ፣ የበቆሎ፣ የዳጉሳ፣ የገብስ፣ የቦለቄ እና ሌሎችም የፍራፍሬ ዓይነቶች ይለማሉ::

የሜካናይዜሽን የእርሻ እንቅስቃሴዎች በስፋት እየተከናወኑ እንደሆነ የገለፁት አቶ አብዱልረህማን፤ በዘንድሮው የመኸር እርሻ ከ80 እና ከ90 በመቶ በላይ መሬት በትራክተር እንደሚታረስና ከአምናው የተሻለ ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱንም ጠቁመዋል::

እየተስተዋለ ያለው የዝናብ መቆራረጥ በመኸር እርሻው አሉታዊ ጫናና የምርት ውስንነትን እንዳያስከትል የተለያዩ አማራጭ ስነ ዘዴዎችን በመጠቀም ከአርሶ አደሩ ጋር በቅንጅት እየተሰራ ስለመሆኑም ምክትል ኃላፊው ገልፀዋል::

በመኸር እርሻው የአትክልትና ፍራፍሬ ችግኞችም በስፋት ሽፋን የሚያገኙ ሲሆን በዚህም የቡና፣ የእንሰት፣ የሙዝ፣ ድንች፣ ቲማቲም እንዲሁም ሌሎችም ይካተቱበታል ሲሉም ተናግረዋል::

የክላስተር እርሻን ለማጎልበትም ከዚህ ቀደም ከነበረው የሄክታር መጠን በላቀ መልኩ የኩታ ገጠም አዝርዕት ሽፋን ባህልን አዳብሮ የማስቀጠል ጥረትም እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በተፈጥሮ ጉዳዮች ምክንያት የምርት መቀነስ እንዳይከሰት ጎን ለጎን የመሬት ለምነትን የሚያጎለብቱ የአፈርና ውሃ ጥበቃ እና የውሃ ማቆሪያ የኩሬ ዝግጅት ሥራዎች በቅንጅት እየተሰሩ ነው ብለዋል ምክትል ኃላፊው::

ከግብርና ግብዓት ጋር በተያያዘ ቀደም ሲል በቂ የዘርና የማዳበሪያ ዝግጅት መደረጉን የገለፁት አቶ አብዱልረህማን፤ ለአርሶ አደሮች በሚያስፈልጋቸው መጠን በወቅቱ የማቅረብ ስራዎች ስለመከናወናቸው ገልፀዋል::

በዞኑ በተለያዩ ወረዳዎች አግኝተን ያነጋገርናቸው አርሶ አደሮች ዘርና ማዳበሪያ በወቅቱ ማግኘታቸውን ገልፀው በመኸር እርሻ የተሻለ ምርት ለማግኘት እየተነቀሳቀሱ እንደሚገኙ ተናግረዋል::

ዘጋቢ: አብዱልሰመድ አወል – ከሆሳዕና ጣቢያችን