ተመራቂ ተማሪዎች በስልጠናው ወቅት የቀሰሙትን እውቀት ወደ ተግባር በመቀየር ለማህበረሰቡ ችግር ፈቺ የምርምር ስራዎችን በማበርከት የድርሻቸውን መወጣት እንደሚጠበቅባቸው ተገለፀ
ግሬት ቪዥን ኮሌጅ በወልቂጤ ካምፓስ ለ6ኛ ዙር በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ያሰለጠናቸውን ከ 310 በላይ ተማሪዎችን በዛሬው እለት በወልቂጤ ከተማ አስመርቋል።
በዚሁ ወቅት የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የጉራጌ ዞን አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊና የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ተወካይ አቶ ደሳለኝ ገብሬ፤ በዓለማችን የበለጸጉ ሀገራት የመጀመሪያ ዕቅዳቸው የተማረ ትውልድ ማፍራት ሲሆን የግሬት ቪዥን ኮሌጅ ይህንን አላማ ለማሳካት የድርሻውን ለመወጣት እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
በዚህም በመደበኛና በማታ መርሀ ግብር ያሰለጠናቸው ተማሪዎችን በዛሬው እለት አስመርቋል።
አክለውም የግል ኮሌጆች ዜጎች በተለያዩ የሙያ መስኮች ራሳቸውን በትምህርት እንዲያሻሽሉ ብሎም ዘመኑን የዋጀ ስራ ወዳድ ትውልድ በመፍጠር ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ሲሆን ግሬት ቪዥን ኮሌጅ አንዱ ነው ብለዋል።
ተመራቂ ተማሪዎች በስልጠናው ወቅት የቀሰሙትን እውቀት ወደ ተግባር በመቀየር ለማህበረሰቡ ችግር ፈቺ የምርምር ስራዎችን በማበርከት የድርሻቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል ሲሉም አቶ ደሳለኝ ገልጸዋል።
የግሬት ቪዥን ኮሌጅ ወልቂጤ ካምፓስ ፕሬዝዳንት ዲላሞ አበበ በበኩላቸው፤ ኮሌጁ በሀዋሳ፣ በሆሳና፣ በወላይታ ሶዶ እና በወልቂጤ ካምፓስ ከፍቶ እያስተማረ ሲሆን በዛሬው እለትም በዲፕሎማ 202 በዲግሪ 108 ሰልጣኞችን ማስመረቁን ተናግረዋል።
ኮሌጁም በዕለቱ ያሰለጠናቸው ተመራቂዎች ወደ አዲስ ስኬት ለመሸጋገር ጅምር ነው በማለት ቀጣይ በስነ-ምግባራቸው የተመሰገኑ እና በሙያቸው ብቁ ሆነው ሀገራቸውን እንዲያገለግሉ አሳስበዋል።
የኮሌጁ አካዳሚክ ፕሬዝዳንት እጩ ዶ/ር ታሪኩ ተክለጻዲቅ፤ ኮሌጁ ላለፉት ስምንት ዓመታት በሁሉም ካምፓሶች በ9 የዲፕሎማ ፕሮግራም ከ5 በላይ በሚሆኑ አጫጭር የስልጠና መርሀ ግብሮች፣ በ3 የመጀመሪያ ዲግሪ ፕሮግራሞች እና በ2 የማስተርስ ዲግሪ በመደበኛና በማታ እንዲሁም በርቀት በማስተማር ለረዥም አመታት ልምድ ያለው መሆኑን አመላክተዋል።
በመማር ማስተማር፣ በማህበረሰብ አገልግሎት እንዲሁም በጥናትና ምርምር በርካታ ስራዎች ሲሰራ መቆየቱን ገልጸው በትምህርት ጥራት ላይ የሚታየው ከፍተት ለመሙላት ከመንግስት ጎን በመሆን በርካታ ተግባራት እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።
የኮሌጁ አመራር እና በሁሉም ደረጃ ያሉት የማኔጅመንት አካላትና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት በጋራ በመሆን ኮሌጁ ለዚህ ስኬት እንዲበቃ የድርሻቸውን መወጣታቸውንም ጠቁመዋል።
ተማሪዎች ለሀገራቸው እድገት ለሚደረገው ርብርብ ተዋናይ በመሆን በማህበራዊ እውቀት ህብረተሰቡን ማገልገል እንዳለባቸውም አውስተዋል።
መንግስት በጀመረው የብልጽግና ጉዞ ተመራቂዎች ከስራ ጠባቂነት ይልቅ ስራን በመፍጠር እንዲሁም በጥቃቅና አነስተኛ የስራ ዘርፎች በመሰማራት ከራስቸው አልፎ ለሌሎች የስራ እድል መፍጠር እንደሚገባቸው ተናግረዋል።
በዕለቱም ከፍተኛ ውጤት በማምጣት የሜዳሊያ ተሸላሚ የሆኑ ተመራቂዎች በሰጡት አስተያየት፤ በኮሌጁ ቆይታቸው በስልጠናው ያገኙትን እውቀት ተግባር ላይ በማዋል ሀገራቸውን እና ማህበረሰቡን ለማገልገል እንደተዘጋጁ ተናግረዋል።
አክለውም በትምህርት ሂደት ውስጥ ችግሮችን ተቋቁመው ለዚህ በመብቃታቸው መደስታቸውን ገልጸዋል።
ዘጋቢ፡ ዝናሽ ሙሉጌታ – ከወልቂጤ ጣቢያችን

More Stories
የአየር ንብረት ለውጥ መቋቋም የሚችል ዘላቂ የግብርና ኢኮኖሚ መገንባት እንደሚገባ ተገለጸ
ከ230 ሺህ በላይ ዜጎች የፋይዳ ዲጅታል መታወቂያ መውሰዳቸውን የሀላባ ዞን ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት መምሪያ አስታወቀ
ብሔራዊ ምክክር ሀገራዊ አንድነትን ከማጠናከር ባሻገር ችግሮችን በውይይትና በሀሳብ የበላይነት ለመፍታት መሠረት እንደሚጥል ተገለጸ