የገጠር ኮሪደር ልማት ስራዎች የአርሶአደሩን አኗኗር ከማሻሻል ባለፈ የዜጎችን ዘላቂ ተጠቃሚነት ለማረጋገጠ የላቀ ሚና እንዳላቸው ተገለፀ

የገጠር ኮሪደር ልማት ስራዎች የአርሶአደሩን አኗኗር ከማሻሻል ባለፈ የዜጎችን ዘላቂ ተጠቃሚነት ለማረጋገጠ የላቀ ሚና እንዳላቸው ተገለፀ

በስልጤ ዞን ምስራቅ አዘርነት በርበሬ ወረዳ የገጠር ኮሪደር ልማት ስራዎችን ለማሳካት ከ35 ሚሊየን ብር በላይ ዕቅድ ተይዞ አዳዲስ ቤቶች የመስራትና የቀደሙትን የማደስ ስራ እየተሰራ መሆኑ ተመላክቷል።

በስልጤ ዞን የምስራቅ አዘርነት በርበሬ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ከይሬ ሀቢብ እንደተናገሩት የገጠር ኮሪደር ልማት የአርሶ አደሩን አኗኗር ከማሻሻል ባለፈ በዘላቂነት የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ያግዛል።

አርሶ አደሮች አጥርና ቤታቸውን ከማሳመር ባለፈ ፖኬጁን አሟልተው እንዲሰሩ አስፈላጊው ድጋፍና ክትትል እየተደረገ መሆኑን ገልፀው ለዚህም ያግዝ ዘንድ እንደ ወረዳው ከ5መቶ ሺህ ብር በላይ ድጎማ መደረጉን አንስተዋል።

እንደ ወረዳው ለመስራት ከታቀዱ 70 ቤቶች ውስጥ 35ቱ መጠናቀቃቸውንና 15 ደግሞ ግንባታቸው በመጠናቀቅ ላይ ያሉ የብሎኬት ቤቶች መኖራቸውን ገልፀዋል።

አርሶ አደሮች ዘመናዊ ቤቶችን ከመገንባትና አካባቢያቸውን ጽዱ ከማድረግ ባለፈ ዝርያቸው የተሻሻሉ የወተት ላሞችና ዶሮዎችን እንዲሁም በጓሯቸው አትክልትና ፍራፍሬ አዲያለሙ አየተደረገ መሆኑንም አክለዋል።

በወረዳው እየተሰሩ ያሉ የኮሪደር ልማት ስራዎች አበረታች እንደሆኑ አስተዳዳሪው አንስተው የተጀመረውን የኮሪደር ልማት ለማፋጠን 35 ሚሊየን ብር ዕቅድ ተይዞ ለተግባሩ ወጤታማነት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው ብለዋል።

የገጠር ኮሪደር ልማትን በላቀ ቁርጠኝነት ለማሳካት እና ውጤታማ ስራዎችን ለመስራት አርሶ አደሩ ተግባራትን በተቀናጀ አግባብ መፈጸም ይኖርበታል ሲሉ ዋና አስተዳዳሪው አቶ ከይሬ ገልፀዋል።

በምስራቅ አዘርነት በርበሬ ወረዳ በአዳዘር ሼበል ቀበሌ ካነጋገርናቸው በገጠር ኮሪደር ልማት ሞዴል ከሆኑ ነዋሪ አርሶ አደሮች መካከል ወ/ሮ ሽፍቴ ኑሪ፣ዋበላ ቡሴር እና ኢማን አብራር እንደተናገሩት የአርሶ አደሩን ህይወት ለመቀየር እየተከናወነ ያለው የገጠር ኮሪደር ልማት ስራ ህይወታቸውን እና አከባቢያቸውን የቀየረ በመሆኑ ደስተኞች መሆናቸውን ገልፀዋል።

ዘጋቢ: ሃጀራ ግርማ – ከሆሳዕና ጣቢያችን