ለአገሪቱ ዘላቂ ሰላምና ዕድገት አሁን እየተካሄደ ያለው ሀገራዊ ምክክር እጅግ ወሳኝና ታሪካዊ ዕድል መሆኑን የሆሳዕና ከተማ የመንግሥት ሠራተኞች ተናገሩ

ለአገሪቱ ዘላቂ ሰላምና ዕድገት አሁን እየተካሄደ ያለው ሀገራዊ ምክክር እጅግ ወሳኝና ታሪካዊ ዕድል መሆኑን የሆሳዕና ከተማ የመንግሥት ሠራተኞች ተናገሩ

የመንግስት ሠራተኞቹ በሰጡት አስተያየት የምክክሩ ስኬታማ እንዲሆን መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሂደቱን የእኔ ነው ብሎ በባለቤትነት ስሜት ሊደግፈውና የበኩሉን አስተዋጽኦ ሊያበረክት እንደሚገባም አሳስበዋል።

በሆሳዕና ከተማ ያነጋገርናቸው አንዳንድ የመንግሥት ሠራተኞች እንደገለፁት፥ ምክክሩ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ያካተተ መሆኑ ሂደቱን ፍጹም ተዓማኒና ውጤታማ እንደሚያደርገው ጠቁመዋል።

በተለይም ባለፉት ዓመታት በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች የተፈጠሩ አለመግባባቶችን በጠረጴዛ ዙሪያ በመወያየት በዘላቂነት ለመፍታት የምክክሩ ፋይዳ የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።

ሠራተኞቹ አያይዘውም ይህ ታላቅ አገራዊ ምክክር ኢትዮጵያ የገጠሟትን ውስብስብ ችግሮች በራሷ ልጆች ጥበብ መፍታት እንደምትችል ለዓለም የሚያሳይና የአገሪቱን ገጽታ ከፍ የሚያደርግ ነው ብለዋል።

በመመካከርና በመደማመጥ አገርን መገንባት እንደሚቻል የገለጹት ሠራተኞቹ፣ የምክክር መድረኩ የኢትዮጵያን አንድነት በጽኑ መሠረት ላይ የሚያቆም መሆኑን ገልጸዋል።

ከምክክሩ የሚሻልና የተሻለ አማራጭ የለንም ያሉት ሠራተኞቹ፥ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ይህንን ዕድል በጸጋ ተቀብሎና የራሱ አድርጎ ለስኬታማነቱ መሥራት እንዳለበት ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ የሁላችንም አገር ናት ያሉት የመንግስት ሠረተኞቹ ስለ አገራችን ሰላምና አንድነት ሲባል ሁሉም ዜጋ የበኩሉን ብሔራዊ ኃላፊነት ሊወጣ ይገባል ብለዋል።

የመንግሥት ሠራተኞቹ ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት የሚጠበቅባቸውን ሙያዊና ዜጋዊ ግዴታ ለመወጣት እንዲሁም ውጤታማነቱን ለማረጋገጥ ዝግጁ መሆናቸውን በቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።

ዘጋቢ: ታምራት አለሙ – ከሆሳዕና ጣቢያችን