በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሆሳዕና ከተማ 6 ሺህ 3 መቶ ካሬ ሜትር መሬት ላይ ከግማሽ ቢሊየን ብር በላይ ወጪ የተገነባውን አለም ማዳበሪያ ከረጢት ፋብሪካ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንዳሸው ጣሰው መርቀው ከፈቱ
ፋብሪካው ከ3 መቶ 50 በላይ ወጣቶችን የስራ ዕድል ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑ ተገልጿል።
በምረቃው ስነ-ስርዓት በክብር እንግድነት የተገኙት ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር)፤ ይህን ግዙፍ ፕሮጀክት ለክልሉ ብሎም ለሀገር ያበረከቱትን ባለሃብት ቤተሰብ አመስግነው ለአካባቢው ነዋሪዎችም የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ፋብሪካው ከአካባቢ አልፎ ሃገርን የሚጠቅም ነው ብለው፤ ከዚህ በኋላ በሚያደርጉት የስራ እንቅስቃሴ እንደክልል ከጎናቸው እንደሚሆኑም አረጋግጠዋል።
ሌሎች ባለሀብቶችም ተሞክሮውን በመውሰድ ለአካባቢያቸውና ለሀገራቸው የበኩላቸውን አሻራ እንዲያሳርፉ ጥሪ አቅርበዋል።
የሀዲያ ዞን ምክትል አስተዳደሪና የዞኑ ገቢዎች መምሪያ ኃላፊ አቶ ደነቀ ጊቻሞ ለእንግዶች የእንኳን ደህና መጣችው መልዕክት ባስተላለፉበት ወቅት፤ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት መተካት የሚለውን የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ኢኒሼቲቪ ተግባራዊ የሚያደርግ ፕሮጀክት መሆኑን ተናግረዋል።
የፋብሪካው ባለቤቶች ወ/ሮ አለምፀሐይ ሰብለወርቅ እና ባለቤታቸው ፀደቀ ግዛቸው ባደረጉት ንግግር፤ ከጥቃቅን ጉሊት ንግድ በመነሳት አሁን ላይ ከ5 መቶ ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የወጣበትን ፋብሪካ መገንባት መቻላቸውን ገልጸዋል።
በፋብሪካው 3 መቶ 50 ወጣቶች የስራ ዕድል ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ከእነዚህም መካከል 80 ከመቶ ሴቶች መሆናቸውን አብራርተዋል።
በምረቃ ስነ-ስርዓቱ የክልሉ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ፋጤ ስርሞሎን ጨምሮ ሌሎች የክልል፣ የሀዲያ ዞንና የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሃገር ሽማግሌዎች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
ዘጋቢ: ሳምራዊት ያዕቆብ – ከሆሳዕና ጣቢያችን

More Stories
የጉራጌ ዞን ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተጠናቀቀው በጀት አመት በዞኑ የተሻለ የልማትና የመልካም አስተዳደር ተግባራት መከናወናቸውን በልዩ ልዩ የክትትል አማራጮች ማረጋገጡን አስታወቀ
በ2018/19 የመኸር እርሻ ወቅት 96 ሺህ ሄክታር መሬት በማልማት ከ8 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማምረት መታቀዱን የጎፋ ዞን ግብርና መምሪያ አስታወቀ
ማሳቸውን ለመኸር እርሻ ደጋግማው በማረስ አለስልሰው በወቅቱ ለመዝራት መዘጋጀታቸውን በከምባታ ዞን ቀዲዳ ጋሜላ ወረዳ ያነጋገርናቸው አንዳንድ አርሶአደሮች ተናገሩ