የአየር ንብረት ለውጥ መቋቋም የሚችል ዘላቂ የግብርና ኢኮኖሚ መገንባት እንደሚገባ ተገለጸ
ሀዋሳ፡ ሐምሌ 10/2018 ዓ.ም(ደሬቴድ) የአየር ንብረት ለውጥ መቋቋም የሚችል ዘላቂ የግብርና ኢኮኖሚ መገንባት ይገባል ሲሉ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር ገለጹ፡፡
በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ አስተባባሪነት ከክልሉ ውኃ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ እንዲሁም ከክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ጋር በመቀናጀት የአዳብቴሽን ፈንድ ፕሮግራም ማስተዋወቂያ እና ስራ ማስጀመሪያ መድረክ በወልቂጤ ከተማ ተካሂዷል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር በመክፈቻ ንግግራቸው፥ የፕሮጀክቱ ዋና ዓላማ ሴቶችን ጨምሮ መላው ማህበረሰብ ያሳተፈ የረጅም ጊዜ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያመጣውን ችግር በብቃት የሚቋቋም፣ ፈጥኖ የሚያገግምና የተላመደ ብዝሀ የገቢ ምንጭ በመፍጠር የምግብና ውሃ ዋስትና ያረጋገጠ ማህበረሰብ መፍጠር እንዲሁም የተሻለ ስነ ምህዳር ማስገኘት ነው ብለዋል።
ፕሮጀክቱ እንደ አገር በስድስት ክልሎች እና በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የም ዞን በፎፋ ወረዳ የሚተገበር ሲሆን፥ የአየር ንብረት ለውጥ መቋቋም የሚችል ዘላቂና አካታች የግብርና ኢኮኖሚ ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ስራውን በቅንጅት ውጤታማ ለማድረግ በመደበኛ ስራ ላይ መተግበር እንደሚገባ አስረድተዋል።
በፍራፍሬ፣ በእንስሳት እርባታ፣ በንብ ማነብ፣ በቅመማቅመም እና በሌሎች ዘርፎች በክልሉ ያሉ ጥሩ የኢንሼቲቭ ተሞክሮዎችን በመውሰድ ፕሮጀክቱን ይበልጥ ውጤታማ ማድረግ ይገባል ብለዋል።
በዚህም ተቋማትና የፕሮጀክቱ ተጠቃሚ ማህበረሰብ በመቀናጀት ሞዴል የግብርና ቤተሰብ መፍጠር እንደሚገባም አሳስበዋል።
ከግብርና ሚንስትር የሲ አር ጂኢ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ሳምሶን እምሩ እና ከገንዘብ ሚንስቴር የዚህ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ዘሪሁን እስጢፋኖስ በመድረኩ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት፥ ፕሮጀክቱ መንግስት ከሚሰራቸው ሰፋፊ መደበኛ የግብርና ስራዎች ባሻገር ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት የተለያዩ የውጭና የሀገር ውስጥ አጋዥ አካላትን በመጠቀም ፍሬያማ ስራ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የም ዞን በፎፋ ወረዳ ሁለት ቀበሌዎች የሚሰራው የአዳፕቴሽን ፈንድ ስራ የማህበረሰቡን የግብርና ስርዓት ለመደገፍ በፕሮግራሙ የተገኘው ግብዓት በአካታችነትና በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ አሳስበዋል።
አክለውም ለስራው ውጤታማነት ጠንካራ የድጋፍና ክትትል ስራ እንደሚሰራ ገልጸዋል።
በመድረኩ የክልሉ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት የአየር ንብረት ለውጥ መቋቋም የሚችል የአረንጓዴ ኢኮኖሚ እውን ለማድረግ በቅንጅት መስራት ይገባል ብለዋል።
ፕሮጀክቱ ለዜጎች ምቹ የስራ እድል ለመፍጠርና የማህበረሰቡን የምግብ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቁመዋል።
ክልሉ በሌሎች ዘርፎች ውጤታማ በመሆን ያሳየውን ተወዳዳሪነት በተጀመረው የአዳፕቴሽን ፈንድ ፕሮግራም የግብርና ስራ ላይ አጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።
በመድረኩ ከገንዘብ እና ግብርና ሚንስቴር የፕሮግራሙ አስተባባሪዎች፣ የማእከላዊ ኢትዮጵያ የክልል፣ የዞንና የወረዳ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
ዘጋቢ፡ አዱኛ ትዕዛዙ – ከወልቂጤ ጣቢያችን

More Stories
ከ230 ሺህ በላይ ዜጎች የፋይዳ ዲጅታል መታወቂያ መውሰዳቸውን የሀላባ ዞን ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት መምሪያ አስታወቀ
ብሔራዊ ምክክር ሀገራዊ አንድነትን ከማጠናከር ባሻገር ችግሮችን በውይይትና በሀሳብ የበላይነት ለመፍታት መሠረት እንደሚጥል ተገለጸ
የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸምና የ2019 ጠቋሚ ዕቅድ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየመከረ ነው