በ2018/19 የመኸር እርሻ ወቅት 96 ሺህ ሄክታር መሬት በማልማት ከ8 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማምረት መታቀዱን የጎፋ ዞን ግብርና መምሪያ አስታወቀ
መምሪያው “ለኢሊኖ (El Niño) ክስተት የማይበገር ግብርናን በመኸር አዝመራ ዕውን እናደርጋለን” በሚል መሪ ቃል የ2018/19 የመኸር ንቅናቄ መድረክን በጎፋ ዞን ጋልማ ከተማ አካሂዷል።
የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኢንጂነር ዳግማዊ አየለ፤ የእርሻ ሥራን ከባህላዊ አሠራር ወደ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ በማሸጋገር ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የተጀመሩ ሥራዎች የበለጠ መጠናከር እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
እንዲሁም የኩታ ገጠም የእርሻ ሥርዓትን ማስፋፋት፣ የመስኖ ልማትን ማጠናከር እና የግብርና ሜካናይዜሽንን በስፋት መጠቀም የዞኑን የግብርና እምቅ አቅም ሙሉ በሙሉ ለመጠቀም እንደሚያስችል ጠቁመዋል።
ከአየር ንብረት መዛባት ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ ችግሮችን ለመቋቋም ተቀናጅቶ መስራት እንደሚገባም አሳስበዋል።
የጎፋ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ዳንኤል ደግፌ በበኩላቸው፤ በዘንድሮው 96 ሺህ ሄክታር መሬት በማልማት ከ8 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማምረት ዕቅድ መያዙን ገልጸዋል።
ኃላፊው ጨምረውም በሌማት ትሩፋት፣ በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ፣ በእንስሳት ሀብት ልማት እና በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን አስረድተዋል።
የጋልማ ከተማ ከንቲባ ኢንጂነር ተስፋለም ነከረ፤ ከከተማው በ5 ኪሎ ሜትር ርቀት የሚገኘው የካውቻ ጥብቅ ደን የአየር ንብረትን ከመጠበቅ ባለፈ የምግብ ዋስትናን፣ ምርትንና ምርታማነትን ለማሳደግ ጠቃሚ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ገልጸዋል።
በመድረኩ የ2018 የመኸር እርሻ አፈጻጸምና የ2019 የመኸር ዕቅድ በግብርና መምሪያው የእርሻ ልማትና የአዝርዕት ሰብሎች ቡድን መሪ አቶ ተስፋዬ ግታ ቀርቦ በባለድርሻ አካላት ውይይት ተደርጎበታል።
ከተሳታፊዎች መካከል አቶ አራሹ አበበ እና አቶ ዮሐንስ በየነ በበልግ ወቅት በአየር ንብረት መዛባት የተከሰተውን የምርት መቀነስ ለማካካስ በመኸር ወቅት ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።
ለኢሊኖ ክስተት ምላሽ በመስጠት በአጭር ጊዜ ምርት የሚሰጡ ሰብሎች፣ የጓሮ አትክልቶችና ሥር ሰብሎች ላይ ትኩረት በመስጠት ችግሩን ለመቋቋም መቻሉን ገልጸዋል።
ዘጋቢ፡ ዓቢይ ይኼይስ – ከሳውላ ጣቢያችን

More Stories
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሆሳዕና ከተማ 6 ሺህ 3 መቶ ካሬ ሜትር መሬት ላይ ከግማሽ ቢሊየን ብር በላይ ወጪ የተገነባውን አለም ማዳበሪያ ከረጢት ፋብሪካ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንዳሸው ጣሰው መርቀው ከፈቱ
ማሳቸውን ለመኸር እርሻ ደጋግማው በማረስ አለስልሰው በወቅቱ ለመዝራት መዘጋጀታቸውን በከምባታ ዞን ቀዲዳ ጋሜላ ወረዳ ያነጋገርናቸው አንዳንድ አርሶአደሮች ተናገሩ
በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በተለያዩ የስራ ዘርፎች ከ40 ሺህ በላይ ወጣቶችን ተሳታፊ በማድረግ 46 ሚሊዮን 620 ሺህ ብር በላይ ከመንግሥት ሊወጣ የሚችለውን ለማዳን ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ጽ/ቤት አስታወቀ