የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ በወልቂጤ ከተማ የሰርከስ ስፖርት ምልመላና የማህበረሰብ አቀፍ የአካል ብቃት መርሃ ግብር ተካሄደ
ሀዋሳ፡ ሐምሌ 09/2018 ዓ.ም(ደሬቴድ) የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ከቀቤና ልዩ ወረዳ ጋር በመተባበር “የታዳጊ ወጣቶች ስፖርት ስልጠና ለበለፀገች ኢትዮጵያ” በሚል መሪ ቃል በወልቂጤ ከተማ የማህበረሰብ አቀፍ የአካል ብቃት እንቅስቃሴና የክልሉ የሰርከስ ስፖርት ዉድድር ለማቋቋም የምልመላ መርሃግብር አካሂዷል።
በክልሉ ባለፉት አመታት በተከናወኑ የስፖርት ልማት ስራዎች የተሻለ ዉጤት መመዝገብ መቻሉን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ አመላክቷል፡፡
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌታቸው ሌሊሾ ስፖርት ወንድማማችነትንና እህታማማችነትን ከማጠናከር በተጨማሪ በአካልና በአይምሮ የዳበረ ሰዉነት ለመገንባት ያለዉ አስተዋፆ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።
ባለፉት አመታት በሁሉም ስፖርት አይነቶች ክልሉን የሚወክሉ ስፖርተኞችን ለማፍራት በተከናወኑ ተግባራት የተሻለ ውጤት መመዝገብ መቻሉን ገልጸዋል።
የቀቤና ልዩ ወረዳ ወጣቶች በሁሉም የስፖርት አይነቶች እያደረጉት ያለዉ ተሳትፎ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባና ልዩ ወረዳዉን ብሎም ክልሉን ሊወክሉ የሚችሉ ስፖርተኞችን መፍጠር እንዲችሉ ቢሮዉ ድጋፍ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል።
የቀቤና ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሐመድ አሚን በደዊ በበኩላቸዉ ስፖርት ለሰላም፣ ለልማትና ህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ለማጎልበት ያለዉ አስተዋጾ የጎላ መሆኑን በመጥቀስ የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ በዘርፉ ዉጤት እንዲመጣ እያደረገ ያለዉ ድጋፍ የሚበረታታ መሆኑን ተናግረዋል።
በርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው ዶ/ር) ሀሳብ አመንጭነት የክልሉን የሰርከስ ስፖርት ቡድን ለማቋቋም ለልዩ ወረዳዉ የተሰጠዉ እድል በመጠቀም በዘርፉ ይበልጥ ዉጤታማ ለመሆን እንደሚሰራም ገልጸዋል።
የተጀመሩ የስፖርት ልማት ስራዎች ለማጠናከር ታዳጊ ወጣቶችና የስፖርቱ ቤተሰብ የክረምት ወራትን በመሰረታዊ የስፖርት ስልጠናና በስፖርት ማዘዉተሪያ ስፍራዎች ማሳለፍ እንደሚገባቸዉም ጠቁመዋል።
የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ምክትል ቢሮና የስፖርት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሰይፈ አለሙ እንደገለጹት በክልልና በአገር አቀፍ ደረጃ ታዳጊ ወጣቶችን በስፖርት ዘርፍ ለማብቃት እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ቢሮዉ በቀቤና ልዩ ወረዳ ክልሉን የሚወክሉ የሰርከስ ቡድን ለማቋቋም የሚያስችል ልዩ የአካል ብቃት ምዘናና የምልመላ መርሃ-ግብር ማከናወኑን ተናግረዋል።
የቀቤና ልዩ ወረዳ ወጣቶችና ስፖርት ጽ/ቤት የስፖርት ዘርፍ ኃላፊ አቶ አብድላ አወል በልዩ ወረዳዉ ባህል እየሆነ የመጣዉን የስፖርት ዘርፍ ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ ለማድረግ ቅንጅታዊ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
የፕሮግራሙ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት በስነ ምግባር የታነጹ ወጣቶችን ለመፍጠር ታዳጊ ወጣቶች ስፖርትን መዉደድና ጊዜያቸዉን በስፖርት ቤቶች ማሳለፍ እንዳለባቸዉ አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ ፡ ሪያድ ሙሂዲን – ከወልቂጤ ጣቢያችን

More Stories
አሰልጣኝ ቶማስ ቱኸል እንግሊዝ ወደ ፍፃሜ ባለማለፏ ከፍተኛ ትችትን አስተናገዱ
ማንቸስተር ዩናይትድ ግብ ጠባቂ አስፈረመ
ማንቸስተር ዩናይትድ አንድሬ ሳንቶስን አስፈረመ