ሀገራችን ኢትዮጵያ በእውቀት፣ በክህሎትና በስነ-ምግባር የበለፀገና የሰለጠነ የነገ ሀገር ተረካቢ ትውልድን ለማፍራት በአዳዲስ ፈጠራና በቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ ትኩረት ሊደረግ ይገባል – ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አንተነህ ፈቃዱ
ሀዋሳ፡ ሐምሌ 04/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) ሀገራችን ኢትዮጵያ በእውቀት፣ በክህሎትና በስነ-ምግባር የበለፀገና የሰለጠነ የነገ ሀገር ተረካቢ ትውልድን ለማፍራት በአዳዲስ ፈጠራና በቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ ትኩረት ሊደረግ እንደሚገባ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር፣ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ እና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንተነህ ፈቃዱ አሳሰቡ።
ወርልድ ብራይት ኮሌጅ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን ከ1 ሺህ 8 መቶ በላይ ተማሪዎችን አስመርቋል።
በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር፣ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ እና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንተነህ ፈቃዱ፤ ተመራቂ ተማሪዎች በትምህርት ቆይታቸው በከፍተኛ ትጋትና ልፋት ያጋጠማቸውን ውጣ ውረድ በብቃት በመወጣትና በትዕግስት ጠንክራው በመስራት ለዚህ ታላቅ የምረቃ ቀን በመብቃታቸው የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ሀገራችን ኢትዮጵያ በእውቀት፣ በክህሎት በስነ-ምግባር የበለፀገና የሰለጠነ የነገ ሀገር ተረካቢ ትውልድን ለማፍራት በፈጠራና በቴክኖሎጂ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ባለበት ወቅት መመረቅ መቻላቸውን ተናግረዋል።
የዕለቱ ተመራቂዎች በኮሌጅ ቆይታችሁ ያገኛችሁትን እውቀት፣ ልምድና ክህሎት ተጠቅማችሁ ስራ ፈጣሪዎች ለመሆን መዘጋጀት እንዳለባቸው አቶ አንተነህ መክረዋል።
ተመራቂዎች ሀገራዊ አንድነት ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ አቶ አንተነህ ጥሪ አቅርበዋል።
ኢትዮጵያን በ2040 ላይ የግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት ለማድረግ የታቀደው ዕቅድ ግብ እንዲመታ ተመርቀው ወደ ስራ የሚሰማሩ ተማሪዎችና የአሁኑ ትውልድ የድርሻቸውን እንዲወጡ አቶ አንተነህ አሳስበዋል።
የወርልድ ብራይት ኮሌጅ ፕሬዚዳንት ተሰማ አበራ (ዶ/ር)፤ ኮሌጁ ለ7 ተከታታይ ዓመታት ተማሪዎችን በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች በማሰልጠን በሀገር ልማትና ዕድገት የድርሻውን እየተወጣ መቆየቱን ገልጸዋል።
ኮሌጁ በዲፕሎማ እና በዲግሪ መርሐ ግብር በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን 1 ሺህ 895 ተማሪዎችን በዕለቱ ማስመረቁንም አስታውቀዋል።
ኮሌጁ ለአካል ጉዳተኛ ተማሪዎችና ለአቅመ ደካማ ተማሪዎች አስፈላጊ ድጋፍ እያደረገ ነውም ብለዋል ዶ/ር ተሰማ።
ኮሌጁን ወደ ዩኒቨርሲቲ ደረጃ በማሳደግ በ2030 በአፍሪካ ደረጃ የልህቀትና የምርምር ማዕከል ለማድረግ እየተሠራ መሆኑንም አስረድተዋል።
ተመራቂዎችም ከኮሌጁ ያገኙትን ዕውቀት ወደተግባር በመቀየርና ስራ በመፍጠር ማህበረሰቡን እንዲያገለግሉ ዶክተር ተሰማ መክረዋል።
ከዕለቱ ተመራቂ ተማሪዎች መካከል ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ የዋንጫ እና የሜዳሊያ ተሸላሚ የሆኑት ተመራቂ ተሰማ ወልዴና ሰብስቤ ደሳለኝ፤ በከፍተኛ ማዕረግ በመመረቃቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።
ተመራቂዎቹ አክለውም፤ በኮሌጁ ቆይታ የቀሰሙትን ዕውቀት ለማህበረሰብ ለውጥ በማዋልና ስራ ፈጥሮ በመስራት ለሀገር አለኝታ ለመሆን እንደሚተጉ ተናግረዋል።
ዘጋቢ: መንግስቱ ፊጣሞ – ከሆሳዕና ጣቢያችን

More Stories
ከ5ሺ በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ በበይነ መረብና በወረቀት እያስፈተነ መሆኑን የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ገለፀ
የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች በተሻሻለ የስልጠና ጥራት፣ በተጠናከረ የኢንዱስትሪ ትስስርና ተፈላጊ ሙያተኞችን በማፍራት በክልሉ ኢኮኖሚ ላይ ተጨባጭ ለውጥ እንዲያመጡ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ቢሮ አስታወቀ
የሀዋሳ ትምህርት ኮሌጅ 4ኛ ዙር ዓመታዊ የጥናትና ምርምር ሲምፖዚዬም አካሄደ