በጎፋ ዞን በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥና ጥራትና ተዓማኒነት ያለው የፍትህ አገልግሎት በመስጠት ረገድ ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውን የዞኑ ፍትህ መምሪያ አስታወቀ

በጎፋ ዞን በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥና ጥራትና ተዓማኒነት ያለው የፍትህ አገልግሎት በመስጠት ረገድ ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውን የዞኑ ፍትህ መምሪያ አስታወቀ

መምሪያው የበጀት ዓመቱን የሥራ አፈጻጸምና በቀጣይ የትኩረት መስኮች ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር የውይይት መድረክ አካሂዷል።

የጎፋ ዞን ፍትህ መምሪያ ኃላፊ አቶ ደመላሽ ብላቴ፤ መምሪያው በበጀት አመቱ ከቀረቡ 5 ሺ 422 ወንጀል መዝገቦች በዐቃቤ ህግ 4 ሺህ 887 መዝገቦች ላይ የተለያዩ አስተያየትና ውሳኔ የተሰጠ ሲሆን ለፍፍር ቤት ከቀረቡ 5 ሺ 734 መዝገቦች ውስጥ በችሎት ክርክር 3 ሺ 588 መዝገብ ጥፋተኛ የተባሉ ሲሆን የማስቀጣት ምጣኔ 91 ነጥብ 1 በመቶ ማከናወን ተችሏል ብለዋል።

በበጀት አመቱ የመንግስትና የሕዝብ ሀብት ለማስመለስ ከቀረቡ 193 የፍትሐብሔር መዝገቦች 14 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር በላይ በህጋዊ ደረሰኝ ወደ መንግስት ካዜና ገቢ ስለመሆኑ አብራርተዋል።

በዞኑ በሁሉም መዋቅሮች በሚገኙ ማረፊያ ቤቶችና ሣውላ ማረሚያ ተቋም በተደረገ ጉብኝት 1 ሺ 519 በቁጥጥር ሥር የዋሉ ተጠርጣሪያዎች በፍርድ ቤት ዋስትናና በግል ዋስትና እንዲለቀቁ እና ምግብና ህክምና ባለበት ማረሚያ ተቋም እንዲቆዩ በማድረግ የዜጎች ሰብዓዊ መብት እንዲከበር ስለመደረጉ አንስተዋል።

በመምሪያው ልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች ዋና ስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ማስረሻ ሰለሞን ባቀረቡት ሪፖርት፤ በበጀት አመቱ በመምሪያውና በታች መዋቅሮች በሁሉም ዘርፎች ውጤት ለማምጣት እና ፈጣን ጥራትና ተዓማኒነት ያለው የፍትህ አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በመምሪያው የሴቶች፣ ህጻናትና ልዩ ምርመራና ክስ ዋና ስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ተፈሪ ትርፌ፤ በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚፈጸሙ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በተለየ ትኩረት ህጋዊ ርምጃ እየተወሰደ ስለመሆኑ ገልጸዋል።

የሴቶችና ህፃናት ልዩ ምርመራና ክስ ጉዳይ ከቀረቡ 466 መዝገብ ውስጥ 461 መዝገብ ክስ የቀረበ ሲሆን በዘርፉ የማጥራት ምጣኔ 98 በመቶ ማከናወን መቻሉን ተናግረዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች ቀልጣፋ የፍትህ አገልግሎት ለህብረተሰቡ በመስጠት የሚፈጠሩ ችግሮችን በጋራ ለማረምና ተጠያቂነት ለማስፈን የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።

በበጀት ዓመቱ የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ መዋቅሮች ዕውቅና የተሰጠ ሲሆን የቀጣይ ዓመት የግብ ስምምነትም ተፈጽሟል።

ዘጋቢ፡ አይናለም ሰለሞን – ከሳውላ ጣቢያችን