የሚዛን ኤፍ.ኤም ወጣቶች የእረፍት ጊዜያቸውን ካልባሌ ቦታዎች በማራቅ በንባብና በጥናት ላይ እንዲያሳልፉ ትልቅ ዕድል መፍጠሩን ገለፀ
ሀዋሳ፡ ሐምሌ 02/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የሚዛን ኤፍኤም 104.5 ሬዲዮ ጣቢያ ያዘጋጀው ነጻ የላይብረሪ አገልግሎት፤ ወጣቶች የእረፍት ጊዜያቸውን ካልባሌ ቦታዎች በማራቅ በንባብና በጥናት ላይ እንዲያሳልፉ ትልቅ ዕድል መፍጠሩን አስታውቋል።
በማዕከሉ እየተጠቀሙ ያሉ ተማሪዎች የንባብ ክፍሉ ፍጹም ጸጥታ የሰፈነበትና ለውጤታማነት እጅግ ምቹ መሆኑን ተናግረዋል።
የሚዛን ኤፍ.ኤም 104.5 ሬዲዮ ጣቢያ በግቢው ውስጥ ያዘጋጀው የንባብ ስፍራ ከድምፅ ረብሻ የጸዳና ተማሪዎች በትምህርታቸው ላይ ሙሉ ትኩረት እንዲሰጡ የሚያግዝ መሆኑን ያነጋገርናቸው ተማሪዎች ገልጸዋል።
ተማሪዎች ከዚህ ቀደም ለንባብና ለጥናት ምቹ ቦታ በማጣት ይቸገሩ እንደነበር ጠቁመው፥ አሁን ላይ የሬዲዮ ጣቢያው የፈጠረው ይህ የላይብረሪ ዕድል ትልቅ እረፍት ከመስጠቱም በላይ በትምህርት ውጤታማነታቸው ላይ ተጨባጭ ለውጥ እያመጣ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ወጣቶች የእረፍት ጊዜያቸውን ያለአግባብ አልባሌ ቦታዎች ላይ ከማባከን ይልቅ እውቀታቸውን የሚገነቡበት ስፍራዎች ላይ ሊያሳልፍ እንደሚገባ ገልፀዋል።
የሚዛን ኤፍኤም 104.5 ሬዲዮ ጣቢያ ለአካባቢው ማህበረሰብ ወቅታዊ፣ አስተማሪና አዝናኝ መረጃዎችን ተደራሽ በማድረግ ከሚሰጠው መደበኛ አገልግሎት ባለፈ፥ አሁን ላይ ሚናውን በማህበራዊ ድጋፍም ጭምር እያሰፋ ይገኛል ያሉት የጣቢያው ምክትል ስራ አስኪያጅ እና የይዘት ዘርፍ ሀላፊ አቶ መኮንን ኢያርዝ ናቸው።
አቶ መኮንን አክለውም አንድ የብዙሃን መገናኛ ተቋም ከዜና እና ፕሮግራም ስርጭት ባለፈ ማህበራዊ ኃላፊነት መወጣት እንዳለበት ጠቅሰው፥ ወጣቶችና ተማሪዎች ነገ ሀገር የሚረከቡ በመሆናቸው የእረፍት ጊዜያቸውን በአልባሌ ስፍራዎች እንዳያባክኑ ምቹ የጥናት ስፍራ መፍጠር የሁላችንም ኃላፊነት ነው ብለዋል።
ጣቢያው ይሄንን የላይብረሪ አገልግሎት ያመቻቸው ወጣቶች የተረጋጋና ከድምፅ ነፃ የሆነ የንባብ ቦታ አግኝተው፥ የንባብ ባህላቸውን እንዲያሳድጉና በትምህርታቸው ውጤታማ እንዲሆኑ ለማስቻል መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፥ በቀጣይም ወቅቱን የዋጁ መፅሀፍቶችን በመለየትና በማደራጅት ለአንባቢያን ይበልጥ ምቹ የማድረግ ስራዎች በትኩረት እንደሚሰሩ አቶ መኮንን ተናግረዋል።
ዘጋቢ፡ ዮናስ ወልደገብሬኤል – ከሚዛን ጣቢያችን
የሚዛን ኤፍ.ኤም ወጣቶች የእረፍት ጊዜያቸውን ካልባሌ ቦታዎች በማራቅ በንባብና በጥናት ላይ እንዲያሳልፉ ትልቅ ዕድል መፍጠሩን ገለፀ

More Stories
ከ4 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ እየሰራ መሆኑን የከምባታ ዞን ገቢዎች መምሪያ አስታወቀ
ከ5ሺ በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ በበይነ መረብና በወረቀት እያስፈተነ መሆኑን የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ገለፀ
የጉራጌ ዞን ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 4ኛ ዙር፣ 13ኛ ዓመት፣ 11ኛ አስቸኳይ ጉባኤውን በወልቂጤ ከተማ እያካሄደ ይገኛል