ለህብረተሰቡ ፈጣን እና ቀልጣፋ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን የሀላባ ቁሊቶ ከተማ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት አስታወቀ

ለህብረተሰቡ ፈጣን እና ቀልጣፋ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን የሀላባ ቁሊቶ ከተማ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት አስታወቀ

ሀዋሳ፡ ሐምሌ 03/2018 ዓ.ም(ደሬቴድ) ለህብረተሰቡ ፈጣን እና ቀልጣፋ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን የሀላባ ቁሊቶ ከተማ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ሥራ አስኪያጅ አቶ ሙባረክ ለማ ገልጸዋል፡፡

በርካታ አገልግሎቶችን ዲጂታል በሆነ መንገድ በአንድ ማዕከል መስጠታቸው ከእንግልትና ጊዜያችንን ከብክነት ታድጎናል ሲሉ አንዳንድ የማዕከሉ ተገልጋዮች ተናግረዋል::

በሀላባ ዞን የቁሊቶ ከተማ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ሥራ አስኪያጅ አቶ ሙባረክ ለማ እንዳሉት፥ ማዕከሉ ሥራ ከጀመረበት ጊዜ ወዲህ በ9 የሥራ መስኮች ቀልጣፋና ፈጣን አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ገልፀዋል::

የፖስታ አገልግሎት፣ የግብር ክፍያ፣ የባንክ፣ የሰነዶች ማረጋገጥ፣ የንግድና ተያያዥ ጉዳዮችን እንዲሁም ሌሎች በርካታ አገልግሎቶችን በአንድ ማዕከል በተቀላጠፈ መንገድ እየሰጠ ስለመሆኑም ጠቁመዋል::

ማዕከሉ በሂደት የአገልግሎት መስኮቹን በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚያሳድግም ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል::

መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ከብልሹ አሠራር፣ ከሙስና እንድሁም ከመልካም አስተዳደር ጉድለቶች የፀዳ አገልግሎት ለህብረተሰቡ ይዞ የቀረበ ጊዜውን የዋጀ ዲጅታል ስርዓት እንደሆነም አመልክተዋል::

ተገልጋዮች የትኛውንም ጉዳይ ከ10 እስከ 20 ደቂቃ ባለው ጊዜ ውስጥ አገልግሎት አግኝተው እንዲጨርሱ እንዳስቻላቸው ኃላፊው አብራርተዋል::

ማዕከሉ በሐምሌ ወር መግቢያ የጀመረውን የግብር ክፍያ እና የንግድ ፈቃድ እድሳት አስመልክቶ ከወትሮ በተለየ መልኩ ለንግዱ ዘርፍ አገልግሎቶች ትኩረት በመስጠት ፈጣንና ቀልጣፋ ዲጂታል አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኝ አቶ ሙባረክ አብራርተዋል።

ማዕከሉ ከንግድ ፈቃድ አገልግሎት በተጨማሪ በገቢ ዘርፍ የቲን ነምበር፣ የሰነዶች ማረጋገጥ እንዲሁም ፋይዳ ምዝገባና ማደስ፣ የፖስታ አገልግሎቶችንና ሌሎች አገልግሎቶችን እየሰጠ እንደሚገኝም አቶ ሙባረክ ጠቅሰዋል።

ያነጋገርናቸው አንዳንድ የማዕከሉ ተገልጋዮች በበኩላቸው አገልግሎቶችን ዲጅታላይዝድ በሆነ መንገድ በአንድ ማዕከል መሰጠታቸው ከእንግልትና ጊዜያችንን ከብክነት ታድጎናል ብለዋል::

ዘጋቢ ፡ አብዱልሰመድ አወል – ከሆሳዕና ጣቢያችን