የተጀመሩ የኢኒሼቲቭ ሥራዎች አበረታች ውጤት እያመጡ መሆኑ ተገለጸ

የተጀመሩ የኢኒሼቲቭ ሥራዎች አበረታች ውጤት እያመጡ መሆኑ ተገለጸ

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ የነባር ኢኒሼቲቮችን የሥራ አፈጻጸምን የገመገመ ሲሆን፥ በ2019 በጀት ዓመት ተግባራዊ በሚደረጉና አዲስ በተቀረጹ የኢኒሼቲቭ ሥራዎች ትግበራ ቅድመ-ዝግጅት ዙሪያ ሰፊ ውይ በማድረግ የቀጣይ የሥራ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የከተማ ልማትና ኢንዱስትሪ ክላስተር አስተባባሪና የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ስንታየሁ ወልደሚካኤል እንዲሁም የቢሮው የተለያዩ የዘርፍ ኃላፊዎች በተገኙበት በዚህ መድረክ፤ ቢሮው በ2018 በጀት ዓመት አቅዶ ያከናወናቸውን ነባር የኢኒሼቲቭ ሥራዎች አፈጻጸምና የአዳዲስ ኢኒሼቲቮች የዕቅድ ዝግጅት ሪፖርትን በዝርዝር ተመልክቷል።

በግምገማውም እንደ አገልግሎት ማዘመን፣ የከተማና የገጠር ኮሪደር ልማት፣ የሁለተኛ ዙር የ“አንድ ከተማ አንድ ፕሮጀክት” ሥራዎች እንዲሁም በመሬት አስተዳደርና ቤቶች ልማት ዘርፎች ላይ የተከናወኑ ተግባራት በጥልቅ ተገምግመዋል።

የተጀመሩት የከተማ ኮሪደር ልማት ስራዎች ፈጥኖ ማጠናቀቅ ፣ የተጓደሉትን ኮንፖነንቶች የሟሟላትና የተጠናቀቁትን የማስተዳደር ስራ ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።

የገጠር ኮሪደር ልማት ስራው ከ75 በመቶ በላይ የገጠር ነዋሪ የኑሮ ዘይቤ ለመቀየር ታልሞ እየተከናወነ የሚገኝ ተግባር በመሆኑ በልዩ ትኩረት መስራት እንደሚገባም አቅጣጫ ተቀምጧል።

በሂደቱም የገጠር መሰረተ ልማትን በማሟላት በፕላን የሚመሩ የገጠር ማዕከላትን ለመፍጠርና የገጠር ትራንስፎርሜሽን አንድ አካል ነው ሲሉም አቶ ስንታየሁ ገልጸዋል።

የገጠር ኮሪደር ልማት የእስካሁን አፈጻጸሙም በአወንታ የተገመገመ ሲሆን ግንባታው የተጀመረባቸው አካባቢዎች በፍጥነት ማከናወን እንዳለባቸውና ያልጀመሩትም ፈጥነው ወደ ስራ መግባት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

የገጠር ኮሪደር ስራው በሚፈለገው መልኩ እንዲጠናቀቅ የልየታ ፣ የግብዓት ና የሀብት አሰባሰብ ንቅናቄ ስራ እና አዳዲስ ቴክኖሎጅዎችን ጥቅም ላይ ለማዋል የተጀመረው ስራ ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባም በመድረኩ ተመላክቷል።

የነባር ኢንሼቲቮች አፈፃፀም ግምገማና በ2019 ተግባራዊ ለማድረግ በመሬት አስተዳደርና ቤቶች ልማት ዘርፎች አዲስ በተቀረጹ ኢንሼቲቮች ትግበራ ቅድመ ዝግጅቶች ዙሪያ ውይይት በማድረግም ቢሮው አቅጣጫ አስቀምጧል።