የሀዋሳ ትምህርት ኮሌጅ 4ኛ ዙር ዓመታዊ የጥናትና ምርምር ሲምፖዚዬም አካሄደ
በሲዳማ ክልል ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ትምህርት ቢሮ የሀዋሳ ትምህርት ኮሌጅ በዛሬው ዕለት 4ኛ ዙር ዓመታዊ የጥናትና ምርምር ሲምፖዚዬም አካሂዷል፡፡
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ በየነ በራሳ በዚህ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፥ ሀገራችንን ከድህነት ለማውጣትና እየተመዘገበ የመጣውን ለውጥ ለማረጋገጥ የበለጠ መትጋ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
በዚህ ሂደት የምሁራን ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልፀው፤ በጥናትና ምርምር በመትጋት ለውጥ አምጪ ሀሳቦችን በማፍለቅ ለሀገሪቱ ያላቸውን አበርክቶ ማሳደግ እንደሚያስፈልግ አመላክተዋል፡፡
በኮሌጁ ያሉ ተማሪዎች፣ ተመራማሪዎች እንዲሁም ከተለያዩ ቦታዎች ተጋብዘው ወረቀቶቻቸውን የሚያቀርቡ ምሁራን ለሀገራቸው እያበረከቱ ላለው አስተዋጽኦ በክልሉ መንግስት ስም አመስግነዋል፡፡
ከዚህም ባሻገር ለትውልድ ጠንክረው መስራት እንደሚጠበቅባቸውና ለሀገር ለውጥ ሊተጉ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
የሀዋሳ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ንጋቱ ቶአሻ በበኩላቸው፥ ዘንድሮ እየተካሄደ ያለው የጥናትና ምርምር 4ኛ ዓመታዊ ሲምፖዚዬም፤ ቴክኖሎጂ የትምህርት ጥራት፣ ለምርምር ልህቀትና ለመምህራን ቀጣይ ላለው የሞያ ዕድገት ምን ያህል አስተዋጽኦ አለው በሚለው ዙሪያ ዓመታዊ የምርምር ስራዎቻችንን አካሂደናል ነው ያሉት፡፡
በሲምፖዚየሙ የተመረጡ የምርምር ጽሁፎች በሀዋሳ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ ተጠንተው አንዳንዶቹ ታትመው በጽሁፍ ተደራሽ የሚሆንበት ሁኔታ ጠቁመው፥ የሚመለከታቸው አካላት እንደዚህ አይነት ሲምፖዚየሞችን በማካሄድ የጥናትና ግኝቶችን ይፋ ማድረግ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ አመላክተዋል፡፡
ጥናቶች ወቅቶችን ጠብቀው ለሚመለከታቸው አካላት ሲደርሱ ሰሚዎቹ ምርምር የሰጣቸውን አካላት ሀሳቦችን በመውሰድ መሰረታዊ ችግሮቻቸውን እንደሚፈቱ ተናግረዋል፡፡
የመድረኩ ተሳታፊ የሆኑት በዲላ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ ብርሐኑ ደንደና (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የጥናትና ምርምር ኮንፍረንሶችና ሲምፖዚዬሞች የትምህርት እድገትና መሻሻሎች ላይ ከፍተኛ ፋይዳ አላቸው ብለዋል፡፡
የሚቀርቡት ጥናትና ምርምሮች ከፍተኛ ትጋት ተደርጎባቸው ተሰርተው የሚመጡ ግኝቶች ስለሆኑ እነዚያ ግኝቶች ደግሞ ወደተግባር ሲቀየሩ የሀገሪቱን የትምህርት አቅጣጫም በመለወጥ ደረጃ የራሳቸው ፋይዳ እንደሚኖራቸው አመላክተዋል፡፡
በመድረኩ ከመላው ሃገራት ከተመረጡ 75 ፕሮፖዛል ቀርበው የተመረጡ 18 የጥናትና ምርምር ስራዎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡
ዘጋቢ፡ ሐና በቀለ

More Stories
ለደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት እና ለቅርንጫፍ ጣቢያ አመራሮችና ጋዜጠኞች የአሠልጣኞች ስልጠና እየተሰጠ ነው
ለሀገራችን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ስኬታማነት ሁሉም የራሱን አስተዋጽኦ ማበርከት አለበት – ኃይለየሱስ ታዬ
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርናና ገጠር ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የመስክ ምልከታ እያካሄደ ነው