የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች በተሻሻለ የስልጠና ጥራት፣ በተጠናከረ የኢንዱስትሪ ትስስርና ተፈላጊ ሙያተኞችን በማፍራት በክልሉ ኢኮኖሚ ላይ ተጨባጭ ለውጥ እንዲያመጡ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ቢሮ አስታወቀ
ቢሮው የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች በውስጣዊ አቅም፣ በአካባቢያዊ ፀጋ እና የገበያ ፍላጎት መሠረት ባደረገ ጥናት ግኝት ትግበራና ተቋማዊ የዕድገት ዕቅድ ዝግጅት ላይ ያተኮረ የንቅናቄና የግንዛቤ መፍጠሪያ መድረክ በወልቂጤ ከተማ አካሂዷል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ቢሮ ምክትልና የተቋማት አቅም ግንባታና ስልጠና ዘርፍ ኃላፊ ኢንጂነር ሰለሞን ፈርሻ እንዳሉት፤ የክልሉን የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ውስጣዊ አቅም በማሳደግ ገበያው የሚፈልገውን የሰው ሀይል ለማፍራት በትኩረት እየተሰራ ነው።
በክልሉ በሚገኙ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ላይ የልየታ ጥናት በማካሄድ የጥናት ዉጤቱም በሚመለከታቸዉ ተቋማት እና ምሁራን ተገምግሞ መፅደቁን ተናግረዋል።
በጥናቱም የየኮሌጁ ውስጣዊ አቅም፣ የሰው ኃይል ሁኔታ፣ የመምህራን ብቃት ማሳደግ፣ የላብራቶሪና የዎርክሾፕ፣ የስልጠና መሳሪያዎች ሁኔታ፣ የየአካባቢው የተፈጥሮ ፀጋ፣ የልማት አቅጣጫዎች፣ የገበያ ፍላጎት፣ የኢንዱስትሪ መስፋፋት እና የወደፊት የክህሎት ፍላጎት መካተቱን አስረድተዋል።
ጥናቱ ዉስን ኃብትን ለመጠቀም፣ የመሳሪያ ግዥን ለማቀናጀት፣ የመምህራን ልማትን ለማጠናከር፣ የኢንዱስትሪ ትስስርን ለማሳደግ እና እያንዳንዱ ኮሌጅ በተለየበት ዘርፍ የላቀ የብቃት ማዕከል እንዲሆን መሠረት የሚጥል መሆኑን ሃላፊው አስረድተዋል።
የየአካባቢውን የኢኮኖሚ አቅም፣ የተፈጥሮ ፀጋ፣ የኢንዱስትሪ ፍላጎት እና የተቋማቱን ውስጣዊ አቅም በመለየት የስልጠና ኮሌጆች በተሻሻለ የስልጠና ጥራት፣ በተጠናከረ የኢንዱስትሪ ትስስር፣ በተፈላጊ ሙያዎች፣ ሥራ ባገኙ እና በፈጠሩ ምሩቃን በክልሉ ኢኮኖሚ ላይ በሚያመጡት ተጨባጭ ለውጦች ላይ ትኩረት ማድረጉንም አመልክተዋል።
የክልሉ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ኢንስቲትዩት ተመራማሪ ዶክተር አበራ ኤልያስ ባቀረቡት ጥናት እንደገለፁት፤ በጥናት የተመሠረተ ልየታ የጥራትና ውጤታማነት መሠረት ነው።
በኮሌጆች በአካባቢያዊ ፀጋ እና በሥራ ገበያ ፍላጎት መሠረት ያደረገ ልየታ ለትክክለኛ ስልጠና፣ ለተፈላጊ ክህሎትና የላቀ ውጤት ለማምጣት እንደሚረዳ ገልፀዋል።
ጥናቱ የኮሌጆች ብቃትና የኢንደስትሪ ፍላጎት እንዲጣጣም በማድረግ ወቅቱ የሚፈልገው የሠው ሀይል ለማፍራት የሚያግዝ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ኮሌጆች የላቀ የብቃት ማእከል እንዲሆኑ መሠረት የሚጥል መሆኑንም በማከል።
የምክክር መድረኩ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት ጥናቱ የአካባቢን ፀጋ በመጠቀም የገበያ ፍላጎትን መሠረት በማድረግ የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እንደሚያግዝ ተናግረዋል።
ሙያን መሠረት ያደረገ ጥራት ያለው ስልጠና ለመስጠት ፋይዳው የጎላ መሆኑን ገልፀው ጥናቱን ተግባራዊ ለማድረግ በቁርጠኝነት መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።
ዘጋቢ፡ ሄኖክ ተክሌ – ከወልቂጤ ጣቢያችን

More Stories
የመምህርነት ሙያ ትውልድን የመቅረፅና ሀገርን የማነፅ ታላቅ የስልጣኔና ማህበራዊ የዜግነት ኃላፊነት በመሆኑ ተመራቂዎች ራሳቸውን ለማብቃት መትጋት አለባቸው – ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አንተነህ ፈቃዱ
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ከ313 ሺህ በላይ የሁለተኛ ደረጃ ይዞታ ማረጋገጫ ሰርተፊኬት ተሰራጭቷል – የክልሉ ግብርና ቢሮ
በመንገድና በድልድይ ግንባታ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ በርካታ ተግባራት መከናወናቸው ተገለፀ