ከ5ሺ በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ በበይነ መረብና በወረቀት እያስፈተነ መሆኑን የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ገለፀ
ሀዋሳ፡ ሐምሌ 01/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) ከ5ሺ 400 በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ በበይነ መረብና በወረቀት እያስፈተነ መሆኑን የወልቂጤ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አብድልሙህሲን ሀሰን ገለጹ፡፡
ዩኒቨርሲቲው የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ በተገኙበት የ12ኛ ክፍል ሃገር አቀፍ ፈተና በዛሬው እለት አስጀምሯል።
የወልቂጤ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አብድልሙህሲን ሀሰን በዚህ ወቅት እንደገለፁት ሀገራችን ለጀመረችው የልማት ጉዞ ስኬት ብቁና የተማረ ሀይል አስፈላጊ በመሆኑ በትምህርቱ ዘርፍ ላይ የሚስተዋለውን ስብራት ለመጠገን በርካታ የሪፎርም ስራዎች ሲሰሩ መቆየቱን አስታውሰዋል።
በትምህርት ዘርፉ ላይ እየተሰሩ ካሉ ስራዎች በዋናነት ኩረጃን ማስቀረት ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፥ በተለይም የ12ኛ ክፍል ተፈታኞች ላይ ትኩረት መደረጉን አንስተዋል።
ሀገር የምትገነባው በመተጋገዝ ሲሰራ ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፥ ዩኒቨርሲቲዎች ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በጋራ በመሆን ተማሪዎችን የማብቃት ስራ ሲሰሩ መቆየታቸውን አንስተዋል።
በዘንድሮው አመት የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ከ3ኛ እስከ ስድስተኛ ዙር ባለው የፈተና መርሀ ግብር ከ5 ሺህ 400 በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ በበይነ መረብና በወረቀት እያስፈተነ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
የፈተናው ደህንነት የተጠበቀ ሆኖ በስኬት ለማጠናቀቅ የመፈተኛ ክፍሎችን የማደራጀት፣ ግብአቶችን የማሟላትና ሌሎችም ቅድመ ዝግጅቶችን በማጠናቀቅ ፈተናው በሰላማዊ መልኩ መስጠት መጀመሩንም አመላክተዋል።
ከ60 በላይ ምቹ የወረቀት ፈተና መስጫ እንዲሁም 35 የበይነ መረብ መፈተኛ ክፍሎች መዘጋጀታቸውን ዶክተር አብድልሙህሲን ጠቁመዋል።
ከመብራትና ከኢንተርኔት መቆራረጥ ጋር ችግሮች እንዳያጋጥሙ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመነጋገር በቂ ዝግጅት መደረጉንና በተጨማሪም በግቢው ውስጥ ከሁለት በላይ ጄነሬተሮች መዘጋጀታቸውን አንስተዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትልና የትምህርት ልማት ዘርፍ ሀላፊ አቶ አስከብር ወልዴ በበኩላቸው እንደ ክልል ተማሪዎች ለፈተና ማዘጋጀትና የፈተና መስጫ ማዕከላት ለማዘጋጀት በርካታ ተግባራት ሲከናወኑ መቆየታቸውን ጠቅሰዋል።
በክልል ደረጃ የዲጂታል ኢንሼቲቭ በማዘጋጀት የፈተና አሰጣጥ ሂደትን ከወረቀት ነፃ ለማድረግ በርካታ ትምህርት ቤቶች በዚህ አመት የበይነ መረብ ፈተና መስጫ ማዕከላት መደረጋቸውን አቶ አስከብር ገልፀዋል።
በክልል ደረጃ ለሶስት አመታት ተማሪ ያላሳለፉ ትምህርት ቤቶችን በመለየት በተለየ መልኩ ድጋፍና ክትትል ሲደረግላቸው እንደቆየም ተናግረዋል።
በሌላ በኩል በክልሉ የሚገኙ የዩኒቨርስቲ መምህራን በሳምንት ቅዳሜና እሁድ ለ12ኛ ክፍል ተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርት ሲሰጡና የፈተና ወረቀቶችን ሲያሰሩ መቆየታቸውን አብራርተዋል።
የዘንድሮው ፈተና የበይነ መረብ ሲስተም በመዘርጋት በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ በቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጆች፣ በአዳሪ ትምህርት ቤቶች እንዲሁም በዩኒቨርሲቲ ማዕከላት ፈተናው የሚሰጥ መሆኑን ጠቁመው፥ በአጠቃላይ እንደ ክልል 61.3 በመቶ የሚሆኑ ተማሪዎች በበይነ መረብ ፈተና ይወስዳሉ ብለዋል።
የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ ሀላፊ አቶ መብራቴ ወልደ ማርያም እንደገለጹት የዘንድሮ ሀገር አቀፍ ፈተና በዞኑ 1ሺህ 578 የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች በ6 ማዕከላት በበይነ መረብና በወረቀት ፈተናው እየወሰዱ መሆኑን አመላክተዋል።
ከሌላ ጊዜ በተለየ መልኩ በተማሪዎች ውጤት ላይ የተመሰረተ ድጋፍ ሲደረግ መቆየቱን ያነሱት ኃላፊው፥ በዞኑ ፈተናውን ለመስጠት አስፈላጊውን የቅድመ ዝግጅት ስራዎች በሰፊው መሰራታቸውን ተናግረዋል።
ፈተናውን ሲወስዱ ያገኘናቸው ተማሪዎች በሰጡን አስተያየትም ዩኒቨርሲቲው ላደረገላቸው ቀና አቀባበል አመስግነው አቀባበሉ ፈተናውን በተረጋጋ መንፈስ ለመስራት እገዛ እንደሚያደርግ ገልፀዋል።
ተማሪዎቹ አክለውም ለፈተናው በቂ ዝግጅት ማድረጋቸውን ጠቁመው ይህም በራሳቸው እንዲተማመኑና ከኩረጃ ነፃ እንዲሆኑ እንዳደረጋቸው ነው ያነሱት።
ዘጋቢ፡ አስፍር ሙህዲን – ከወልቂጤ ጣቢያችን

More Stories
የጉራጌ ዞን ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 4ኛ ዙር፣ 13ኛ ዓመት፣ 11ኛ አስቸኳይ ጉባኤውን በወልቂጤ ከተማ እያካሄደ ይገኛል
የመምህርነት ሙያ ትውልድን የመቅረፅና ሀገርን የማነፅ ታላቅ የስልጣኔና ማህበራዊ የዜግነት ኃላፊነት በመሆኑ ተመራቂዎች ራሳቸውን ለማብቃት መትጋት አለባቸው – ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አንተነህ ፈቃዱ
የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች በተሻሻለ የስልጠና ጥራት፣ በተጠናከረ የኢንዱስትሪ ትስስርና ተፈላጊ ሙያተኞችን በማፍራት በክልሉ ኢኮኖሚ ላይ ተጨባጭ ለውጥ እንዲያመጡ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ቢሮ አስታወቀ