የጉራጌ ዞን ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 4ኛ ዙር፣ 13ኛ ዓመት፣ 11ኛ አስቸኳይ ጉባኤውን በወልቂጤ ከተማ እያካሄደ ይገኛል
በዞኑ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ፍፁም ነጻ፣ ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ ሆኖ መጠናቀቁ ተምሳሌት ዞን ለመፍጠር የሚደረገውን ጉዞ የሚያግዝ መሆኑን የምክር ቤቱ ዋና አፈ ጉባኤ አቶ ኸይሩ መሀመድ ገለፁ።
የጉራጌ ዞን ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ ኸይሩ መሀመድ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር፤ በሀገሪቱ የተካሄደውን 7ኛው ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ በዞኑ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና የሕዝብ የነቃ ተሳትፎ የታየበት ሆኖ መጠናቀቁን ገልጸዋል።
ለምርጫው ስኬታማነት እናቶች፣ አባቶች፣ ወጣቶች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና እጩዎች እንዲሁም በየደረጃው የሚገኙ የፀጥታ አካላት ያበረከቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ በመሆኑ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በምርጫው ሂደት በዞኑ በሁሉም አካባቢዎች የታየው የሕዝብ መነቃቃት፣ ትብብር፣ ቁርጠኝነትና ቅንጅት በዞኑ የተጀመረውን የለውጥና የዕድገት ጉዞ አጠናክሮ ለማስቀጠል ትልቅ መሠረት የጣለ መሆኑንም አስገንዝበዋል አቶ ኸይሩ።
ከምርጫው ማግስት ጀምሮ የዞኑ አመራር ሳይዘናጋ ሕዝብ የሚያነሳቸውን እና በበጀት ዓመቱ የታቀዱ የልማት፣ የመልካም አስተዳደርና የፍትሕ ጥያቄዎችን ለመመለስ ወደ ተግባር በመግባት ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን ማረጋገጥ ተችሏል ብለዋል።
የዞኑ ሕዝብ ከአመራሩ ጋር በመቀናጀት የአካባቢውን ሰላም በዘላቂነት በማስጠበቅ ሁለንተናዊ የልማት እንቅስቃሴዎች ይበልጥ ማፋጠን ይጠበቅበታል ብለዋል ዋና አፈ ጉባኤው።
አክለውም የተጀመረውን ሀገራዊ የምክክር ሂደት ለሀገሪቱ ሰላምና አብሮነት ወሳኝ ሚና ይጫወታል ብለዋል።
በሀገራችን ለዘመናት ሲያወዛግቡ የነበሩ፣ ሀገራዊ በጎ ገጽታን የሚያጠለሹ በውስጥ ባንዳዎችና በውጭ ታሪካዊ ጠላቶቻችን ለፖለቲካ መጠቀሚያ ሲሆኑ የነበሩ አጀንዳዎችን በውይይት ለመፍታት ይህ የምክክር መድረክ ትልቅ ዕድል እንደሚሰጥ አብራርተዋል።
ዘጋቢ፡ ሪድዋን ሰፋ – ከወልቂጤ ጣቢያችን

More Stories
ህዝበ ሙስሊሙ የመውሊድ በዓልን ሲያከብር በብዝሃነት ውስጥ የሚንፀባረቁ የመረዳዳትና የአብሮነት በጎ እሴቶችን ይበልጥ በማጠናከር ሊሆን እንደሚገባ ተገለጸ
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ኃላፊና የየዞን ከፍተኛ አመራሮች በሣውላ ማረሚያ ተቋም አረንጓዴ አሻራቸውን በማኖር ልዩ ልዩ የልማት ሥራዎችን ጎበኙ
በጌዴኦ ዞን ይርጋጨፌ ወረዳ የማህጸን በር ጫፍ ካንሰር ምርመራ እና ልየታ ተካሄደ