ማርከስ ራሽፎርድ ወደ ማንችስተር ዩናይትድ ይመለሳል
ማንችስተር ዩናይትድ የዘንድሮውን የቅድመ-ውድድር ዘመን ዝግጅቱን በይፋ ሲጀምር የፊት መስመር ተጫዋቹ ማርከስ ራሽፎርድ በቡድኑ ስብስብ ውስጥ እንደሚካተት ተረጋግጧል።
ከባርሴሎና ጋር የነበረውን የውሰት ውል ያጠናቀቀው ራሽፎርድ፤ አዲሱ የክለቡ ዋና አሰልጣኝ ማይክል ካሪክ ባቀዱት አዲስ ፕሮጀክት ውስጥ ወሳኝ ሚና ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል።
ማይክል ካሪክ በጥር ወር የክለቡን መሪነት ከተረከቡ በኋላ ቡድኑን ወደ ቻምፒዮንስ ሊግ በመመለስ አስደናቂ ለውጥ አሳይተዋል።
አሰልጣኙ በግላቸው ከራሽፎርድ ጋር ምንም አይነት ችግር እንደሌለባቸው የገለጹ ሲሆን፤ ተጫዋቹ ከእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ጋር በዓለም ዋንጫው ላይ ካሳለፈው ጊዜ በኋላ በቀጥታ ወደ ኦልትራፎርድ እንዲመለስ እቅድ እንደተያዘለት ዘጋርዲያን አስነብቧል።
በዘገባው መሰረት የቀድሞው አሰልጣኝ ሩበን አሞሪም በነበሩበት ወቅት በሁለቱ ወገኖች መካከል ተፈጥሮ የነበረው መቃቃር የተረሳ ታሪክ ሆኗል።
ራሽፎርድ አሁን ትኩረቱ ሙሉ በሙሉ በወደፊት የውድድር ዘመን ላይ ነው።
አሰልጣኝ ማይክል ካሪክ በክለቡ ድረ-ገጽ ላይ እንደገለጹት፤ “ቡድኑ ከማንኛውም ሊጉ ውስጥ ካሉ ተቀናቃኞች ጋር መፎካከር የሚችል አቅም አለው። አሁን ትኩረታችን ይህን ብቃት ለሙሉ የውድድር ዘመን ማሳየት እና ለዋንጫ መዋጋት ላይ ነው“በማለት ለደጋፊዎቹ ቃል ገብተዋል።
በቅርቡ የቅድመ ውድደር ዘመን ዝግጅቱን የሚጀምረው ዩናይትድ ዝግጅቱን ሜዳ ላይ ከማከናወኑ በተጨማሪ ስድስት የአቋም መለኪያ ጨዋታዎችን ያደርጋል።
ማርከስ ራሽፎርድ በዓለም ዋንጫው ከእንግሊዝ ቡድን ጋር እስከ ፍጻሜው የሚቆይ ከሆነ ወደ ልምምድ የሚመለስበት ነሐሴ ወር መጀመሪያ ይሆናል።
በስፔን ቆይታው የባርሴሎናን የላ ሊጋ ዋንጫ በማሳካት አሻራውን ያሳረፈው ራሽፎርድ፤ ምንም እንኳን ዩናይትድ ከፍተኛ ደሞዙን ለመቀነስ ፍላጎት ቢኖረውም በአሁኑ ሰዓት ተጫዋቹን የሚፈልጉ ተገቢ ክለቦች ባለመኖራቸው በኦልትራፎርድ የሚኖረው ቆይታ ይቀጥላል።
አሰልጣኝ ማይክል ካሪክ በተጫዋቹ ችሎታ ላይ እምነት ያላቸው በመሆኑ፤ ራሽፎርድ አዲስ የራስ መተማመንን ገንብቶ ለዩናይትድ ስኬት የበኩሉን አስተዋፅኦ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።
ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ
ማርከስ ራሽፎርድ ወደ ማንችስተር ዩናይትድ ይመለሳል

More Stories
ማንቸስተር ዩናይትድ ግብ ጠባቂ አስፈረመ
ማንቸስተር ዩናይትድ አንድሬ ሳንቶስን አስፈረመ
የ2018 የCBE የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ እና የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪሚየር ሊግ ውድድርን በማሸነፍ ሁለት ዋንጫ ላነሳው የሲዳማ ቡና እግር ኳስ ክለብ ክልሉ ያዘጋጀውን የዕውቅናና የሽልማት ፕሮግራም ዛሬ ሰኞ ሐምሌ 06/2018 ከቀኑ 12፡00 ጀምሮ በሀዋሳ ሀይሌ ሪዞርት ይካሄዳል።