በዞኑ ከ11ሺ 268 የደረጃ “ለ” ግብር ከፋዮች ከ56.8 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ መታቀዱ ተገለፀ

በዞኑ ከ11ሺ 268 የደረጃ “ለ” ግብር ከፋዮች ከ56.8 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ መታቀዱ ተገለፀ

ሀዋሳ፡ ሐምሌ 01/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) በዞኑ ከ11ሺ 268 የደረጃ “ለ” ግብር ከፋዮች ከ56.8 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ መታቀዱን የካምባታ ዞን ገቢዎች መምሪያ ገለፀ።

“ግብር ለሀገር ክብር ገቢ ለልማት” በሚል መሪ ቃል የ2018 ዓ.ም የደረጃ “ለ” ግብር መክፈያ መርሃ-ግብር በካምባታ ዞን ሺንሽቾ ከተማ በይፋ ተጀምሯል።

ግብርን በወቅቱና በታማኝነት በመክፈል የዜግነት ግዴታቸውን እየተወጡ መሆናቸውን ግብር ከፋዮች ተናግረዋል።

ግብርን በወቅቱ መክፈል ለሀገር ሁለንተናዊ ልማት ያለው ፋይዳ የጎላ ነው።

በደረጃ “ለ” ግብር መክፈያ ማስጀመሪያ መርሐግብሩ ላይ የተገኙት የካምባታ ዞን ገቢዎች መምሪያ ኃላፊ አቶ አሰፋ ካሰሞ ባስተላለፉት መልዕክት፥ በዞኑ ሁሉም አከባቢዎች የተጀመረውን የገቢ አሰባሰብ ሂደት ያለ ምንም መንጠባጠብ በታማኝነትና በወቅቱ የመክፈል ኃላፊነት የሁሉም ግብር ክፋዮች ግደታ መሆኑን አመላክተዋል።

በዞኑ በአጠቃላይ የደረጃ “ለ” ግብር ከፋዮች ቁጥር 11ሺ 268 መሆኑን የገለፁት አቶ አሰፋ፥ ከነዚህ ግብር ከፋዮች 56.8 ሚሊየን ብር ለመሰብሰብ መታቀዱን አስረድተዋል።

በሺንሽቾ ከተማ ያነጋገርናቸው የህብረተሰብ ክፍሎች በሰጡን አስተያየት ግብርን በጊዜ በመክፈል የዜግነት ግዴታቸውን ከመወጣትም ባሻገር ለአከባቢው ብሎም ለሀገር ልማት አሻራቸውን ለማስቀመጥ በወቅቱ እየከፈሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የሚፈለገው ልማትና ብልፅግና እንዲረጋገጥ በቀጣይም የድርሻቸውን እንዲወጡ ገልጸዋል፡፡

በማስጀመርያ መርኃ ግብሩ ላይ የከምባታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አረጋ እሸቱን ጨምሮ የዞኑ አስተባባሪ አካላት፣ የሺንሸቾ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ መለሰ ገብሬ እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካለት ተገኝተዋል ።

ዘጋቢ፡ አለማየሁ ማተቦ – ከሆሳዕና ጣቢያችን