የሜሲ እንባ

ሊዮኔል ሜሲን በተመለከተ ሁሌም የሚነሳ አንድ የጥርጣሬ ነጥብ ቢኖር፣ በስሜት መለዋወጥ ረገድ ያለውን መቀዛቀዝ ነበር።

በሜዳ ላይ ያለው መረጋጋቱ፣ ትርምስን ሰንጥቆ የሚያልፍበት የጨዋታ ጥበቡ፣ አንዳንዴም ከሰው ልጅ ስሜት የራቀ፣ እንደ ሮቦት የሚያስቆጥረው መረጋጋት ብዙዎች ሲያደንቁት የኖሩት ነው።

ነገር ግን፣ ትናንት ምሽት አልቢሴሌስቲዎቹ ግብፅን 3-2 በረቱበት መርሐግብር ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኋላ ሜሲ እንባውን መቆጣጠር ሲያቅተው የታየበት ትዕይንት፣ ለዓመታት የነበረውን ይህንን አመለካከት በአንዴ ቀይሮታል።

ይህ እንባ፣ የሜሲን ስሜታዊነት ብቻ ሳይሆን፣ ለአርጀንቲና ማሊያ ያለው ጥልቅ ፍቅር እና ለድል ያለው የማይጠገብ ጥማት ማሳያ ነበር።

ጨዋታው ለተመልካች የማይረሳ ትዕይንት ነበር። ግብፅ በያሰር ኢብራሂም የጭንቅላት ኳስ እና በሙስጠፋ ዚኮ ግብ 2-0 በመምራት፣ በታላቋ አርጀንቲና ላይ ድንቅ የሜዳ ላይ ስራ እየሰራች ነበር። እስከ 79ኛው ደቂቃ ድረስ ግብፅ ድሉን እንደጨበጠች ታስብ ነበር።

ሆኖም የአርጀንቲና ትልቁ ጥንካሬ በውድድሩ እያሳየችው ያለው የማይናወጥ መረጋጋት ነው።

አሰልጣኝ ሊዮኔል ስካሎኒ በቡድኑ ላይ ያደረጉት ቅያሬዎች እና ተጫዋቾቹ በጭንቅ ሰዓት እንኳን የነበራቸው ክህሎት፣ ጨዋታውን ወደ ተአምራዊ ቅፅበት ቀይረውታል።

ሜሲ በአብዛኛው የጨዋታው ክፍል ሲንቀሳቀስ የነበረው እንደ ቀድሞው በጉልበት ሳይሆን፣ በብልሃት ነበር።

የዘንድሮው ሜሲ የጨዋታ ስልት በቅጽበታዊ ብልጭታዎች የተገነባ ነው።

በምሽቱ ጨዋታ ምንም እንኳ በመጀሪያው አጋማሽ የፍፁም ቅጣት ምት ቢያመክንም ከእሱ እግር ተነስታ ለክርስቲያን ሮሜሮ የተመቻቸችው የጭንቅላት ኳስ፣ በግብፅ ተከላካዮች ላይ ሽብርን ፈጠረች።

ከዚያም በግሩም ሁኔታ ያስቆጠራት የአቻነት ግብ፣ ሜዳውን በጩኸት አደበላለቀችው።

በመጨረሻም የሁለቱ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች በድካም በተቃወሰ መንፈስ ውስጥ ሆነው ሳለ፣ ኤንዞ ፈርናንዴዝ ለአርጄንቲና የአሸናፊነት ግብን አስቆጥሮ ጨዋታው ሲጠናቀቅ፣ ሊዮኔል ሜሲ ስሜቱን መቆጣጠር ተስኖት አይኑ እምባ አፈለቀ።

ይህ እምባው የሽንፈት ሳይሆን የሀገር ፍቅር እና የአልሸነፍ ባይነት እንጂ!

አርጀንቲና በምሽቱ ጨዋታ ያን ያህል የሚያምር እግር ኳስ አልተጫወተችም።

ነገር ግን፣ ባለፉት ውድድሮች እና እንደ ኬፕ ቨርዴ ካሉ ጨዋታዎች የተማረችው ትልቁ ትምህርት አለ፡ በጭንቅ ጊዜ መረጋጋት።

ሜሲ ሜዳ ላይ በነበረበት ጊዜ ሁሉ የነበረው የረጋ መንፈስ፣ ጨዋታው ሲያልቅ ወደ እንባ የተቀየረው፣ ለአርጀንቲና ማሊያ የሚከፍለው መስዋዕትነት ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ለማሳየት ነው።

ሜሲ ከአሁን በኋላ ስሜቱን ለመደበቅ አይሞክርም፤ ምክንያቱም ያ እንባ የድል ጣፋጭነት እና የሀገር ፍቅር መገለጫ ነው።

ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ