የመምህርነት ሙያ ትውልድን የመቅረፅና ሀገርን የማነፅ ታላቅ የስልጣኔና ማህበራዊ የዜግነት ኃላፊነት በመሆኑ ተመራቂዎች ራሳቸውን ለማብቃት መትጋት አለባቸው – ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አንተነህ ፈቃዱ
ሀዋሳ፡ ሰኔ 27/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የመምህርነት ሙያ ትውልድን የመቅረፅና ሀገርን የማነፅ ታላቅ የስልጣኔና ማህበራዊ የዜግነት ኃላፊነት በመሆኑ ተመራቂዎች ራሳቸውን ለማብቃት መትጋት እንዳለባቸው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንተነህ ፈቃዱ ገለፁ።
የሆሳዕና ትምህርት ኮሌጅ በተለያዩ የትምህርት መስኮች በዲግሪ፣ በዲፕሎማና በሰርተፊኬት መርሃ-ግብር ያስተማራቸውን 1051ተማሪዎችን ለ20ኛ ዙር አስመርቋል።
በምረቃ መርሃ-ግብሩ ላይ በክብር እንግድነት ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንተነህ ፈቃዱ፤ በትምህርቱ ዘርፍ ኮሌጁ ለበርካታ ዓመታት የተሰጠውን ሀላፊነት በአግባቡ እየተወጣ እንደሚገኝ ጠቅሰው ከትምህርት ተደራሽነት ባሻገር በጥራት ዙሪያ ለተሰጠው ትኩረት የተመራቂዎች ሚና ላቅ ያለ መሆኑን ገልፀዋል።
የመምህርነት ሙያ ትውልድን የመቅረፅ፣ ሀገርን የማነፅ ታላቅ የስልጣኔና የተቀደሰ ማህበራዊ የዜግነት ሀላፊነት በመሆኑ አዳዲስ ዕውቀቶችንና ክህሎቶችን በማሰስ ራስን ለማብቃት መትጋት እንዳለባቸውም አቶ አንተነህ አሳስበዋል።
ሀገራችን ለያዘችው ራዕይ የዕለቱ ተመራቂዎች የበኩላቸውን የዜግነት አስተዋጽኦ ለማበርከት መዘጋጀት እንዳለባቸው የጠቆሙት አቶ አንተነህ፤ በተመረቁበት የሙያ መስክ ስራ በመፍጠር መንቀሳቀስ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
የሆሳዕና ትምህርት ኮሌጅ ዲን አባይነህ ኤርጎጎ (ዶ/ር) የእንኳን ደህና መጣችሁ ብለው፤ የዕለቱ ተመራቂ ተማሪዎች ከአመታት ድካምና ልፋት በኋላ ለዛሬ ፍሬ በመብቃታቸው እንኳን ደስ ያላችሁ ብለዋል።
የአንድ ነገር ፍጻሜ የሌላ ነገር ጅማሬ በመሆኑ ተመራቂ ተማሪዎች ከፊት ለፊታቸው ለሚያጋጥመው አዲስና የተለየ ምዕራፍ ራሳቸውን ማዘጋጀት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ኮሌጁ በምርምና ማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራትን በማከናወን የተቋቋመበትን ዓላማ እያሳካ እንደሚገኝ ያነሱት ዶ/ር አባይነህ፤ የኮሌጁን የመማር ማስተማር ሂደት ከማዘመንና ከማጠናከር ባለፈ የክልሉን የትምህርት ችግሮች ለመፍታት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል ብለዋል።
ተማሪዎች በተማሩበት ሙያ ሀገራቸውንና ህዝባቸውን በትጋትና በታማኝነት እንዲያገለግሉም ዶ/ር አባይነህ ለተመራቂ ተማሪዎች መልዕክት አስተላልፈዋል።
በምረቃው ፕሮግራም ያነጋገርናቸው አንዳንድ ተመራቂ ተማሪዎች በትምህርት ወቅት ያገኙትን እውቀትና ክህሎት ለሀገራቸው ዕድገት ለማዋል ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የእለቱ እንግዶች በኮሌጁ ችግኝ ተከላ አካሂደዋል።
ዘጋቢ: ዳኜ አየለ – ከሆሳዕና ጣቢያችን

More Stories
የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች በተሻሻለ የስልጠና ጥራት፣ በተጠናከረ የኢንዱስትሪ ትስስርና ተፈላጊ ሙያተኞችን በማፍራት በክልሉ ኢኮኖሚ ላይ ተጨባጭ ለውጥ እንዲያመጡ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ቢሮ አስታወቀ
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ከ313 ሺህ በላይ የሁለተኛ ደረጃ ይዞታ ማረጋገጫ ሰርተፊኬት ተሰራጭቷል – የክልሉ ግብርና ቢሮ
በመንገድና በድልድይ ግንባታ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ በርካታ ተግባራት መከናወናቸው ተገለፀ