በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የደረጃ “ሀ” እና “ለ” ግብር ከፋዮች የ2019 በጀት ዓመት ዓመታዊ የግብር ክፍያና የንግድ ሥራ ፍቃድ ዕድሳት በሳውላ ከተማ በይፋ ተጀምሯል
በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ዓለምነሽ ደመቀ፤ የግብር አሰባሰቡን በማዘመንና በተገቢው መንገድ ግብር በመሰብሰብ የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን ማፋጠን እንደሚቻል ገልጸዋል።
እንደ ኃላፊዋ ገለጻ፤ በክልሉ በገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 65/2018 መሠረት 7 ሺህ 330 የደረጃ “ሀ” እና 121 ሺህ 745 የደረጃ “ለ” ግብር ከፋዮች ይገኛሉ። ከሐምሌ 01/2018 ዓ.ም እስከ ጥቅምት 30/2019 ዓ.ም ባለው የግብር መክፈያ ጊዜም 13.834 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ መታቀዱን አስታውቀዋል።
በክልሉ ከሚገኙት 136 የታክስ ማዕከላት ውስጥ 105ቱ በቴክኖሎጂ የተደገፉ ሲሆን፤ 90 ማዕከላት የቴሌብር አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን ገልጸዋል። በተጨማሪም 101 አዳዲስ የአገልግሎት ማዕከላት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኢንጂነር ዳግማዊ አየለ በበኩላቸው፤ ግብርን በታማኝነትና በወቅቱ መክፈል የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን ለማፋጠን ወሳኝ መሆኑን ገልጸው ሁሉም ግብር ከፋዮች የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
የሳውላ ከተማ ከንቲባ አቶ በላይነህ ባህሩ፤ በ2019 በጀት ዓመት ከመደበኛና ከማዘጋጃ ቤት አገልግሎቶች ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ መታቀዱን ገልጸው ግብር ከፋዮች ግብራቸውን በወቅቱና በአግባቡ በመክፈል ለከተማውና ለሀገሪቱ ልማት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ጥሪ አቅርበዋል።
በሳውላ ከተማ ያነጋገርናቸው የደረጃ “ሀ” እና “ለ” ግብር ከፋዮችም ዓመታዊ ግብራቸውን በወቅቱ እየከፈሉ መሆናቸውን ገልጸው ግብር በአግባቡ መክፈል የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን ለማፋጠን አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።
ዘጋቢ፡ ስንታየሁ ሙላቱ – ከሳውላ ጣቢያችን

More Stories
ማሳቸውን ለመኸር እርሻ ደጋግማው በማረስ አለስልሰው በወቅቱ ለመዝራት መዘጋጀታቸውን በከምባታ ዞን ቀዲዳ ጋሜላ ወረዳ ያነጋገርናቸው አንዳንድ አርሶአደሮች ተናገሩ
በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በተለያዩ የስራ ዘርፎች ከ40 ሺህ በላይ ወጣቶችን ተሳታፊ በማድረግ 46 ሚሊዮን 620 ሺህ ብር በላይ ከመንግሥት ሊወጣ የሚችለውን ለማዳን ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ጽ/ቤት አስታወቀ
የቀቤና ልዩ ወረዳ ማህበረሰብ የልማት ፍላጎት ማሟላት የሚቻለው ግብርና ታክስ በታማኝነትና በወቅቱ መክፈል ሲቻል መሆኑ ተገለጸ