ግብር በወቅቱ መክፈል አካባቢንና ሀገርን የመለወጥ አቅሙ ከፍተኛ መሆኑ ተገለጸ
ሀዋሳ፡ ሐምሌ 01/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) ግብር በወቅቱ መክፈል አካባቢንና ሀገርን የመለወጥ አቅሙ ከፍተኛ መሆኑን ሁሉም የንግዱ ማህበረሰብ በወቅቱና በታማኝነት እንዲከፍል የሀድያ ዞን አስተዳዳር ጥሪ አቀረበ።
በወረዳው የሚገኙ 855 የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮች ሐምሌ 1 ቀን 2018 ዓ.ም በአንድ ቀን ውስጥ ግብር ከፍለው እንዲያጠናቅቁ እየተሰራ መሆኑንም የሌሞ ወረዳ ገቢዎች ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።
የወረዳውን የገቢ አሰባሰብ ንቅናቄ በበሌሳ ታዳጊ ማዘጋጃ ቤት በይፋ ያስጀመሩት የሌሞ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታደለ ደምሴ፤ ግብር ለሀገር ዕድገትና ልማት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
ግብር ከፋዮች የሚጠበቅባቸውን ግብር በወቅቱና በታማኝነት በመክፈል ለሀገር ብልጽግና የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከት እንዳለበት አሳስበዋል።
በእስካሁኑ ሂደት ወረዳው በግብር አሰባሰብ ግንባር ቀደም እንዲሆን የንግዱ ማህበረሰብ የተለመደውን ተግባር እንዲያጠናክርም ጥሪ አቅርበዋል።
የሌሞ ወረዳ ገቢዎች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሽፈራው አለቃ በበኩላቸው፤ በወረዳው የሚገኙ 855 የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮች በአንድ ቀን ውስጥ ግብራቸውን አጠናቀው እንዲከፍሉ የሚያስችል ዕቅድ መያዙን ጠቁመዋል።
በ2018 በጀት ዓመት 339 ሚሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ ታቅዶ 294 ሚሊዮን 63 ሺህ 500 ብር መሰብሰብ መቻሉን ጠቁመው፥ በ2019 በጀት ዓመት ከመደበኛና ከማዘጋጃ ቤታዊ ገቢ 350 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ ስራ መጀመሩን ገልጸዋል።
ከዚህ ውስጥ 4 ሚሊዮን 555 ሺህ ብር ከደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮች የሚሰበሰብ መሆኑን ጠቁመዋል።
ሐምሌ 1 ቀን 2018 ዓ.ም ከማለዳው 12 ሰዓት ጀምሮ በወረዳው በሚገኙ በሁሉም ማዕከላት ግብር መሰብሰብ መጀመሩን ገልጸው ሁሉም ግብር ከፋዮች በተቀመጡት ቀናት ውስጥ ግዴታቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል ብለዋል።
የሀድያ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የገቢዎች መምሪያ ኃላፊ አቶ ደነቀ ጊቻሞ በበኩላቸው፤ ግብር መክፈል አካባቢንና ሀገርን የመለወጥ አቅም ያለው መሆኑን ገልጸው፣ የንግዱ ማህበረሰብ በታማኝነት እንዲንቀሳቀሱ ጥሪ አቅርበዋል።
የሌሞ ወረዳ ለዞኑ ገቢ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ በመሆኑ ሊበረታታ እንደሚገባ ጠቅሰው፣ የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮችም ክፍያውን በአጭር ጊዜ በማጠናቀቅ ግንባር ቀደም እንዲሆኑ አሳስበዋል።
በዞኑ ደረጃ በ2018 በጀት ዓመት ከ7 ነጥብ 39 ቢሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ ታቅዶ እስካሁን ባለው ሂደት ከ6 ነጥብ 35 ቢሊዮን ብር ከዕቅዱ 92 ከመቶ በላይ ማሳካት መቻሉን አቶ ደነቀ ገልጸዋል።
በ2019 በጀት ዓመት ደግሞ ከ8 ቢሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን ጠቁመዋል።
አንዳንድ ግብር ከፋዮች በበኩላቸው፤ የሚከፍሉት ግብር ለመንግስት የልማት ሥራዎች የሚውል መሆኑን በመረዳት ግብራቸውን በወቅቱና በታማኝነት እየከፈሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ዘጋቢ: ታምራት አለሙ – ከሆሳዕና ጣቢያችን

More Stories
በዞኑ ከ11ሺ 268 የደረጃ “ለ” ግብር ከፋዮች ከ56.8 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ መታቀዱ ተገለፀ
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የደረጃ “ሀ” እና “ለ” ግብር ከፋዮች የ2019 በጀት ዓመት ዓመታዊ የግብር ክፍያና የንግድ ሥራ ፍቃድ ዕድሳት በሳውላ ከተማ በይፋ ተጀምሯል
በክልሉ የደረጃ “ለ” እና “ሀ” ግብር ከፋዮች ግብር የመክፈያ ጊዜ ይፋ ማድረጉን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ገቢዎች ቢሮ ገልጿል