በክልሉ ለተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎች የተቀናጀ የማህበራዊ ጥበቃና ድጋፍ ስርዓትን ማጠናከር እንደሚገባ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የማህበረሰብ አቀፍ ድጋፍና ክብካቤ ጥምረትና በተጋላጭ ልየታ ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ በሳውላ ከተማ ተካሂዷል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ካሴች ኤሊያስ መድረኩን ሲከፍቱ፤ መንግስት የዜጎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለማቃለል እና ድህነትን ለማስወገድ ህዝቡ በየደረጃው የሚሳተፍበትና የሚጠቀምበት ድሃን ማዕከል ያደረገ፣ ፈጣን፣ ተከታታይ እና ዘላቂ ልማትን ማረጋገጥ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በመደበኛ እና መደበኛ ባልሆነ መንገድ ድህነትን፣ የዜጐችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ስጋት፣ ተጋላጭነትን እና መገለልን ለመቀነስ የሚያስችል እርምጃ በመውሰድ ለሁሉም ተደራሽ የሆነ የተመጣጠነ እድገት ለማረጋገጥ መትጋት ይገባል ብለዋል።
በዋነኝነት በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ አደጋ፣ በኢኮኖሚና በማህበራዊ ችግሮች ምክንያት ለከፋ ችግር ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች በተቀናጀ ሁኔታ ጥበቃ እንዲያገኙ የማድረግ፣ ዜጎች ለተለያዩ ችግሮች እንዳይጋለጡ መከላከል ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
የቢሮው ምክትል ኃላፊና የማህበራዊ ዘርፍ ኃላፊ ወ/ሮ ምህረት በላይ በበኩላቸው፤ የማህበራዊ ዋስትና ስርዓትን የመዘርጋት፣ የዜጎችን ሰርቶ የማግኘትና ጥሪት የመያዝ አቅምን የማጎልበት፣ የሥራ ዕድልና የኑሮ ሁኔታን የማሻሻል እና ለጥቃትና በደል ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን የህግ ጥበቃና ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆን ያስፈልጋል ብለዋል።
ተጋላጮችን መደገፍና ኑሯቸውን ማሻሻል ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመፈጸም ከክልል ጀምሮ እስከ ወረዳ ድረስ ይህንን የሚያስተባብር ማህበራዊ ጥበቃ አስተባባሪና ቴክኒክ ኮሚቴ በማቋቋም እና በቀበሌ ደረጃ ደግሞ የማህበረሰብ አቀፍ ድጋፍና ክብካቤ ጥምረት በማደራጀት እንደሚፈጸም አስረድተዋል።
በቀበሌ ማህበረሰብ አቀፍ ድጋፍና ክብካቤ ጥምረት ላይ እና የተጋላጭ ልየታ ላይ በቢሮው የማህበራዊ ችግሮች መከላከል ዳይሬክቶረት አቶ አግዜ ናራዶ እንዲሁም በመረጃ መሰብሰቢያ ፎርማት ላይ በቢሮው የማህበራዊ ጥበቃ ባለሙያ አቶ አመኑ እራሴ ቀርቦ ውይይት ተካሂዷል።
የመድረኩ ተሳታፊዎች ሀሳብና አስተያየት ሰጥተው ከመድረኩ ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቷል።
ዘጋቢ፡ አይናለም ሰለሞን – ከሳውላ ጣቢያችን

More Stories
የአርባምንጭ ከተማ ሰላማዊና በተፈጥሮ ፀጋ የበለፀገለች መሆኗ ለቱሪዝም ዘርፍ ተመራጭ ያደርጋታል – የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዴኤታ አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ
የሀለባ ዞን ምክር ቤት ለ2019 በጀት ዓመት ከ3 ቢልዮን 293 ሚልዮን ብር ባለይ በጀት አጸደቀ
መስራት እየቻሉ የገንዘብ እጥረት የገጠማቸው የህብረተሰብ ክፍሎችን ችግሮች ለመፍታት የህብረት ስራ ማህበራት ሚና ቀላል አለመሆኑ ተገለጸ