በክልሉ የደረጃ “ለ” እና “ሀ” ግብር ከፋዮች ግብር የመክፈያ ጊዜ ይፋ ማድረጉን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ገቢዎች ቢሮ ገልጿል
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ቀመሪያ ረሻድ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ በክልሉ ያለውን ዘላቂ የልማትና የመሠረተ ልማት ፍላጎቶች በራስ አቅም ለመሸፈንና የፋይናንስ አቅምን ለማሳደግ ሰፊና የተቀናጁ ሥራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡
የዕቅድ አፈጻጸም በተመለከተ በ2018 በጀት ዓመት 27 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ፣ እስከ ሰኔ 29 ቀን ድረስ ከ26 ቢሊዮን ብር በላይ (ከ96 በመቶ በላይ) ገቢ መሰብሰብ ተችሏል ብለዋል።
በበጀት ዓመቱ ከ26 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡንም ቢሮው ያስታወቀ ሲሆን የገቢዎች የደረጃ “ሀ” እና “ለ” ግብር ከፋዮች የመክፈያ ወቅትም ይፋ ሆኗል።
የገቢ አፈጻጸሙ ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፍተኛ ዕድገት እያሳየ መምጣቱን ጠቁመዋል፡፡
በክልሉ በአጠቃላይ 115,794 ግብር ከፋዮች ያሉ ሲሆን፤ ከእነዚህም ውስጥ 5,481ዱ የደረጃ “ሀ”፣ 110,313ቱ ደግሞ የደረጃ “ለ” ግብር ከፋዮች መሆናቸውንም አስታውቀዋል።
የደረጃ “ለ” እና “ሀ” ግብር ከፋዮች የ2018 በጀት ዓመት ዓመታዊ ግብራቸውን ከመጪው ከሐምሌ 1 እስከ ሐምሌ 10 ቀን 2018 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ግብራቸውን ከፍለው እንዲያጠናቅቁ አስታውቀዋል።
ከሕግ ማስከበርና ቁጥጥር ጋር በተያያዘ ጠንካራ የግብር ሕጎችን የማስከበር፣ የኦዲትና የቁጥጥር ሥርዓቶች በተገቢው መንገድ መተግበራቸውን ጨምሮ የግብር ከፋዩን ግንዛቤ በማሳደግ በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የግብር መክፈል ባሕል እንዲጎለብት መደረጉን አስታውቀዋል።
አገልግሎቱን ከማዘመን ጋር ተያይዞ ነጋዴው ባለበት ሆኖ ግብሩን በቀላሉ መክፈል የሚያስችለው የኢ-ፔይመንት (e-payment) ሥርዓት መጀመሩን ተናግረዋል።
ቢሮው ግብር ከፋዮች ያለምንም እንግልት፣ ፈጣን፣ ቀልጣፋና ተደራሽ አገልግሎት በየአቅራቢያቸው እንዲያገኙ ሁሉንም አስፈላጊ ቅድመ ዝግጅቶች ማጠናቀቁን ወይዘሮ ቀመሪያ ገልጸዋል።
በመሆኑም ግብር ከፋዮች የተመቻቸውን ምቹ ሁኔታና ሰፊ አማራጮች በመጠቀም ካላስፈላጊ መስተጓጎል ቅጣትና ወለድ በመዳን ግብራቸውን በተቀመጠው የጊዜ ገደብ (ከሐምሌ 1 እስከ 10) እንዲከፍሉና ለክልሉ ልማትና ለሕዝብ ጥያቄዎች ምላሽ መገኘት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
ለተመዘገበው ከፍተኛ ውጤት አስተዋጽኦ ላበረከቱት ግብር ከፋዮች ለንግዱ ማኅበረሰብ ለባለድርሻ አካላትና ሌሊት ከቀን አብረው ለሠሩ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት በራሳቸውና በቢሮው ስም ላቅ ያለ ምስጋና አቅርበዋል።
ለከፍተኛ ገቢ አሰባሰብ ውጤቱ መመዝገብ በቅንጅት የተሰሩ ስራዎች ውጤት እንዳስገኙ የገለጹት ቢሮ ኃላፊዋ፤ ከክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጀምሮ እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ ያለው ጠንካራ የቅንጅት ሥራና የአመራሩ ቁርጠኝነት ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው ተናግረዋል።
ዘጋቢ፡ ብሩክ አማረ

More Stories
በክልሉ ለተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎች የተቀናጀ የማህበራዊ ጥበቃና ድጋፍ ስርዓትን ማጠናከር እንደሚገባ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ ከ2 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ መቻሉን የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ጽ/ቤት አስታወቀ
በ230 ሚሊዬን ብር ወጪ ለግብርና ልማት ጠቃሚ ቁሳቁሶች ድጋፍ ማድረጉን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ግብርና ቢሮ የምግብ ሥርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም ገለጸ