በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ ከ2 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ መቻሉን የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ጽ/ቤት አስታወቀ

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ ከ2 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ መቻሉን የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ጽ/ቤት አስታወቀ

በከተማ አሰተዳደሩ የ2018 የግብር አሰባሰብ እና የንግድ ፍቃድ ዕድሳት ማስጀመሪያ የንቅናቄ መድረክ ተካሂዷል።

መድረኩን በንግግር ያስጀመሩት የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አውላቸው ዮሐንስ፤ በከተማው የሚሰበሰበው ገቢ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ገልጸዋል።

በበጀት ዓመቱ 2 ነጥብ 88 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ ለመጀመሪያ ጊዜ ከ2 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ የተሰበሰበ ሲሆን ይህም ባለፈው ዓመት ከተሰበሰበው ጋር ሲነጻጸር ከአንድ ቢሊየን ብር በላይ ብልጫ ያለው መሆኑን ተናግረዋል።

ለገቢው መጨመርም ከዚህ ቀደም ገቢ የማይሰበሰብባቸውን ዘርፎች ለይቶ ወደ ግብር ስርዓት ማስገባት፣ ዉዝፍ ዕዳዎች እንዲከፈሉ ማድረግ፣ የዞኑን ዋና አስተዳዳሪን ጨምሮ ሌሎች አመራሮችና ባለሙያዎች በቅንጅት በመስራታቸው መሆኑንም ገልጸዋል።

በከተማ አስተዳደሩ ከ12 ሺህ በላይ ግብር ከፋዮች መኖራቸውን የገለጹት አቶ አዉላቸዉ፤ ለተገልጋዩ ህብረተሰብ ደረሰኝ መስጠት ሲገባቸዉ ያልሰጡ 140 ግብር ካፋዮች እያንዳንዳቸው አንድ መቶ ሺህ ብር እንዲቀጡ በማድረግ አስተዳደራዊ እርምጃዎች መውሰዳቸውንም ገልጸዋል።

በቀጣይ የክረምት ወራት ከመደበኛና ከማዘጋጃ ቤታዊ ገቢዎች ከ170 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ መታቀዱንና ለዚህም ከሐምሌ 1 ጀምሮ ወደ ተግባር ለመግባት በቴክኖሎጂ የታገዘ በቂ ዝግጅት ስለመደረጉ ጠቅሰዋል።

ግብር ከፋዮች ተገቢውን ደረሰኝ በመስጠትና ግብርን በወቅቱ በመክፈል አስፈላጊ ላልሆነ ቅጣትና ወለድ መዳረግ እንደሌለባቸውም ኃላፊው አሳስበዋል።

የሆሣዕና ከተማ አስተዳደር ንግድና ገበያ ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አይናለም ይርዳው በበኩላቸው፤ እንደ ከተማ አስተዳደሩ ከሐምሌ አንድ ጀምሮ ከ9 ሺህ 370 በላይ ነባር ነጋዴዎች የንግድ ፍቃድ እንዲያድሱ ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር የቅንጅት ስራዎች መጠናቀቃቸውን ገልጸዋል።

የሆሣዕና ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሽጉጤ እንዳሉት፤ እንደከተማ አስተዳደር ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰበሰበው ገቢ በቅንጅት ከተሰራ ማንኛውንም ነገር ማሳካት እንደሚቻል ማሳያ ነው።

በ2019 በጀት ዓመት ከ3 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ መታቀዱን የጠቆሙት ከንቲባው፤ በዚህም በከተማው የተጀመሩ ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎችን በማጠናቀቅ አዳዲስ ልማቶችን እናስጀምራለን ሲሉም ገልጸዋል።

በመድረኩ የተገኙት የሀዲያ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማቲዮስ አኒዮ በበኩላቸው፤ በሆሣዕና ከተማ በአሁኑ ጊዜ በርካታ የልማት ስራዎች በተሰበሰበው ገቢ እየተከናወኑ መሆናቸውን ገልጸው ለዚህም የከተማ አስተዳደሩ ህዝቡን በማስተባበር ምሽት ጭምር እየሰራ ያለው ስራ የሚደነቅ መሆኑን ተናግረዋል።

አሁንም ቢሆን የህብረተሰቡን የልማት ፍላጎት ለማሟላት ገቢን በአግባቡ መሰብሰብ ወሳኝ በመሆኑ ሐምሌ 1 የሚጀመረው የግብር አሰባሰብ እና የንግድ ፈቃድ ዕድሳት ስራዎች በተቀናጀ መልኩ መመራት እንዳለበትም ዋና አስተዳዳሪው አሳስበዋል።

በመድረኩ የተሳተፉ ባለድርሻ አካላትም በገቢ አሰባሰብም ሆነ በንግድ ፍቃድ ዕድሳት ዙሪያ በክረምት ወራት ለመስራት የታቀዱ ተግባራትን ለማሳካት በቅንጅት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

ዘጋቢ: ተሻለ ከበደ – ከሆሳዕና ጣቢያችን