ሀዋሳ፡ ሰኔ 26/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል እየተተገበረ ባለው የሁለተኛ ደረጃ መሬት ልኬትና ምዝገባ ስራ 217ሺህ 703 አርሶአደሮችን የሰርተፊኬት ባለቤት ማድረግ መቻሉም ተገልጿል።
በቢሮው የተፈጥሮ ሀብት ልማት ፤መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ውብሸት ዘነበ እንደገለጹት፤ ቀደም ሲል በአንደኛ ደረጃ ምዝገባ ወቅት በወረቀት ላይ ሰፍሮ የነበረውን መረጃ ወደ ዲጂታል ስርዓት የመቀየር ሰፊ ስራ እየተከናወነ ይገኛል።
ይህ አሰራር የመሬት መረጃዎች የጠሩና ዘመናዊ እንዲሆኑ ከማድረግ ባለፈ፣ የአርሶአደሩን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል።
የሁለተኛ ደረጃ ይዞታ ማረጋገጫ ካርታ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ እያደረገ እንደሚገኝ የገለጹት አቶ ውብሸት፤ በዚህም 39 ሚሊዮን 562 ሺህ 900 ብር ብድር ማግኘት ችለዋል።
በክልሉ ግብርና ቢሮ የመሬት አስተዳደር እና አጠቃቀም ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አበበ ታደሰ በበኩላቸው፤ መሬት ትልቁ ሀብት መሆኑን ገልጸው ለዚህም ዘመናዊ የመረጃ ስርዓት መዘርጋት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።
በክልሉ ካሉ 41 የገጠር ወረዳዎች ውስጥ 22ቱ በሁለተኛ ደረጃ ልኬት መሸፈናቸውን ገልጸዋል።
380ሺህ ማሳዎችን በመለካት 313 ሺህ 129 የይዞታ ማረጋገጫ ሰርተፊኬቶችን ለ217ሺህ 703 አርሶአደሮች መሰራጨቱን ገልጸዋል፡፡
ከእዚህ ውስጥ 248ሺህ 570 ማሳዎችን ወደ ብሔራዊ የገጠር መሬት መረጃ ማዕከል ማሸጋገር መቻሉንም ተናግረዋል ።
በአሁኑ ወቅት ልኬት ላይ የሚገኙ 8 ወረዳዎች መኖራቸውን የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ አዲስ አሰራር በመዘርጋት የወረቀት ምዝገባን በማስቀረት በሞቫይል መተግበሪያ በሚታገዘ ቀልጣፋ አሰራር ሙሉ በሙሉ ለመተካት እየተሰራ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ይህን ዘመናዊ አሰራር በላቀ ደረጃ ለማስቀጠል ለባለሙያዎች REILA (Responsible and Innovative Land administration) በተባለ በፊንላንድ መንግስት ድጋፍ በተግባር የተደገፈ ስልጠና እየተሰጠ ይገኛል ሲሉም ገልጸዋል።
ከሰልጣኝ ባለሙያዎች መካከል አቶ ምትኩ ይገዙ፣ ወይዘሪት ሚዛን መሸሻ እና ቀሲስ ሰለሞን ወንድሙ በሰጡት አስተያየት፤ ስልጠናው ስራቸውን በብዙ መልኩ የሚያግዝ መሆኑን ገልጸው፣ የአርሶ አደሩን የግብርና ፋይናንስ ተጠቃሚነት ለማሳደግ ወሳኝ ነው ብለዋል።
ይህ ስልጠና የቡና ማሳዎች እና በደን የተሸፈኑ አከባቢዎች ላይ የሁለተኛ ደረጃ የመሬት ልኬት ስራዎችን በጥራት ለመስራት ያስችላልም ብለዋል፡፡
የቀሰሙትን እውቀት ወደ ታችኛው መዋቅር ለማውረድ ዝግጁ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል።
በመጨረሻም ምክትል ቢሮ ኃላፊዉ አቶ ውብሸት ዘነበ ፤ ለሁለተኛ ደረጃ የመሬት ልኬትና ምዝገባ ስኬት እንደ CALM P for R፣ SLM P እና REILA ያሉ ፕሮጀክቶች ከፍተኛ ድጋፍ እያደረጉ እንደሚገኙ ገልጸው ምስጋና አቅርበዋል ።
ዘጋቢ፡ በትዕግስቱ ጴጥሮስ – ከቦንጋ ጣቢያችን

More Stories
በመንገድና በድልድይ ግንባታ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ በርካታ ተግባራት መከናወናቸው ተገለፀ
ሀገራዊ ምክክር፤ የመደማመጥ፣ የመግባባትና የጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ መሠረት ነው!
ከ23 ሚሊየን በላይ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች እንደሚተከሉ ተገለጸ