በ230 ሚሊዬን ብር ወጪ ለግብርና ልማት ጠቃሚ ቁሳቁሶች ድጋፍ ማድረጉን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ግብርና ቢሮ የምግብ ሥርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም ገለጸ
ሀዋሳ፡ ሰኔ 29/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) እየተጠናቀቀ ባለው በጀት ዓመት ለክልሉ ግብርና ዘርፍ ዕድገት አጋዥ የሆኑ ተሽከርካሪዎችን ጨምሮ ለግብርና ልማት ጠቃሚ ቁሳቁሶችን 230 ሚሊዬን ብር ወጪ በማድረግ ለ6 ዞኖችና ለ15 ወረዳዎች ማከፋፈሉን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ግብርና ቢሮ የምግብ ሥርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም (FSRP) አስታወቀ።
ፕሮግራሙ ለክልሉ ምርትና ምርታማነት ማደግ የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን ገልጿል።
በክልሉ ግብርና ቢሮ የምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም (FRSP) ማኔጅመንት ዩኒት ስራ አስኪያጅ አቶ ወንድወሰን ሁሴን እንደገለጹት የፕሮግራሙ ዓላማ የምግብ ሥርዓትን የመቋቋም አቅምን ማሳደግና የምግብ ዋስትና ችግር እንዳይፈጠር የመከላከል አቅምን ማሻሻል ነው።
እየተጠናቀቀ ባለው በጀት ዓመት ብቻ 18 የመስክ መኪኖች፣ 172 ሞተር ሳይክሎች፣ ስድስት የሩዝ መፈልፈያ ማሺኖች፣ አንድ የአነስተኛ ጥልቅ ጉድጓድ መቆፈሪያ ማሽንና ሌሎች ለግብርና ልማት ማደግ እገዛ የሚያደርጉ ቁሳቁሶችን በክልሉ ለሚገኙ ስድስት ዞኖችና 15 የፕሮግራም ወረዳዎች ማከፋሉን አስረድተዋል።
ለነዚህም ወደ 230 ሚሊዬን ብር ወጪ መደረጉን ገልጸው፤ በዚህም የፌደራሉ የምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም አስተዋፅኦ ማድረጉን ተናግረዋል።
ፕሮግራሙ የአርሶ-አደሩንና የባለሙያውን አቅም ለማሳደግ በየጊዜው የአቅም ግንባታ ስልጠና መስጠቱንም ገልጸዋል።
በክልሉ ወደ ሙሉ ትግበራ ከገባበት 2016 ዓመተ-ምህረት ጀምሮ ወደ 738 ሚሊዬን ብር በመመደብ ለግብርናው ምርትና ምርታማነት ዕድገት ወሳኝ የሆኑ 116 የተለያዩ ዓይነት የገጠር መሰረተ-ልማት ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ወደ ልማት እንዲገቡና አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረጉን አስታውቀዋል።
ዘጋቢ፡ ብዙአየሁ ጫካ – ከቦንጋ ጣቢያችን

More Stories
የአርባምንጭ ከተማ ሰላማዊና በተፈጥሮ ፀጋ የበለፀገለች መሆኗ ለቱሪዝም ዘርፍ ተመራጭ ያደርጋታል – የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዴኤታ አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ
የሀለባ ዞን ምክር ቤት ለ2019 በጀት ዓመት ከ3 ቢልዮን 293 ሚልዮን ብር ባለይ በጀት አጸደቀ
መስራት እየቻሉ የገንዘብ እጥረት የገጠማቸው የህብረተሰብ ክፍሎችን ችግሮች ለመፍታት የህብረት ስራ ማህበራት ሚና ቀላል አለመሆኑ ተገለጸ