የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ገቢዎች ቢሮ ከደረጃ ግብር ከፋዮች ከ13.8 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ማቀዱን ገለጸ
ሀዋሳ: ሰኔ 28/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ገቢዎች ቢሮ ከደረጃ “ሀ “እና “ለ” ግብር ከፋዮች ከ13.8 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ቅድመዝግጅት ማጠናቁን አስታውቋል።
ግብር ከፋዮች ግብራቸውን በፍትሃዊነት እንዲከፍሉ ከማዕከላዊ ስታትስቲክ መረጃዎችን በመውሰድ የዋጋ ግሽበት ማስተካከያ መደረጉም ታውቋል፡፡
ቢሮው የ2018 ግብር ዘመን የገቢ አሰባሰብን በማስመልከት ለሚዲያዎች መግለጫ ሰጥቷል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ አለምነሽ ደመቀ ለሚዲያዎች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፥ መላውን የክልሉን ግብር ከፋይ ለ2018 የግብር ዘመን እንኳን አደረሳችሁ ብለው በክልሉ 7 ሺህ 330 የደረጃ “ሀ”እና 121 ሺህ 745 ደረጃ “ለ”ግብር ከፋዮች እንደሚገኙ ጠቁመዋል ፡፡
በክልሉ የገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 65/2018 መሠረት የክልሉ ደረጃ “ሀ” እና “ለ” ግብር ከፋዮች ዓመታዊ የግብር ግዴታቸዉን ከሃምሌ 1 ጀምሮ የሚወጡበት ነዉ ብለዋል::
በክልሉ 121ሺህ 745 ደረጃ “ለ”ግብር ከፋዮች የሚገኙ ሲሆን ከሐምሌ 1 ቀን 2018 እስከ ሐምሌ 30 ቀን 2018 ዓም የግብር ግዴታቸውን የሚወጡ ቢሆንም በ10 ቀን ውስጥ ቀድሞ ለማጠናቀቅ ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁንም አክለዋል።
7 ሺህ 330 የደረጃ “ሀ” ግብር ከፋዮች ከሀምሌ 1 ቀን 2018 ዓ.ም እስከ ጥቅምት 30 ቀን 2019 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ዓመታዊ ግብራቸውን እንደሚከፍሉ ኃላፊዋ አብራርተዋል።
እነዚህ ግብር ከፋዮች የ2018 የግብር ዘመን ዓመታዊ ግብራቸውን ምቹና ተደራሽ በሆነ መንገድ መክፈል እንዲችሉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ተሰርተዋል፡፡
ግብር ከፋዮች ግብራቸውን በፍትሃዊነት እንዲከፍሉ ከማዕከላዊ ስታትስቲክ መረጃዎችን በመውሰድ የዋጋ ግሽበት ማስተካከያ መደረጉን ወ/ሮ አለምነሽ ገልጸዋል፡፡
በዚህም በክልሉ ከሚገኙ 136 የታክስ ማዕከላት ውስጥ በ105ቱ የተቀናጀ የመንግስት ታክስ አስተዳደር ስርዓት
በቴክኖሎጂ ተደራሽ በመሆኑ ግብር ከፋዮች ባሉበት ሆነዉ የሚከፍሉባቸዉ አማራጮች መዘጋጀታቸውን ጠቁመዋል።
ግብር ከፋዮች የተቀመጡትን አማራጮች በመጠቀም ዓመታዊ ግብራቸውን በሚከፍሉበት ጊዜ የሚገጥም የኔት ወርክ መቆራረጥ ችግርን ለመቅረፍ ቅድመዝግጅት መደረጉንም አብራርተዋል።
በአጠቃላይ በክልሉ ከሐምሌ 1 ቀን 2018 እስከ ጥቅምት 30 ቀን 2019 ዓ.ም ባሉት የዓመታዊ ግብር መክፈያ ጊዜ ውስጥ 13.834 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ እየሰራ ነው።
በክልሉ የሚገኙ ግብር ከፋዮች የተቀመጡ የክፍያ አማራጮችን በመጠቀም በመንግስት ለተያዙ የልማት ዕቅዶች ተግባራዊነት የበኩላችውን ድርሻ እንዲወጡ ኃላፊዋ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ ፡ አሰግድ ተረፈ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን

More Stories
በጎፋ ዞን በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ1 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብስቡን የዞኑ ገቢዎች መምሪያ አስታወቀ
የህብረተሰቡን የልማት ፍላጎት ለማሟላት ዞኑ የሚያመነጨውን ገቢ አሟጦ መሰብሰብ እንደሚገባ የአሪ ዞን አሰተዳደር አስታወቀ
የሀዲያ ዞን ምክር ቤት 2.8 ቢሊየን ብር ተጨማሪ በጀት አጸደቀ