የህብረተሰቡን የልማት ፍላጎት ለማሟላት ዞኑ የሚያመነጨውን ገቢ አሟጦ መሰብሰብ እንደሚገባ የአሪ ዞን አሰተዳደር አስታወቀ
በዞኑ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ1.2 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ መቻሉም ተመላክቷል፡፡
የዞኑ ገቢዎች መምሪያ ከንግድና ኢንዱስትሪ ልማት መምሪያ ጋር በመቀናጀት የ2018 ግብር ዘመን ማስከፈያ እንዲሁም የ2019 ዓ.ም የንግድ እድሳት ማስጀመሪያ የንቅናቄ መድረክ በጂንካ ከተማ አካሂዷል፡፡
በምክክር መድረኩ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የአሪ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብረሃም አታ፤ የህብረተሰቡን የልማት ፍላጎት ለማሟላት በዞኑ ዉስጥ ያሉ የገቢ አማራጮችን በተገቢዉ መንገድ አሟጦ መሰብሰብ እንደሚገባ ገልፀዋል።
ለስራዉ ስኬታማነት አመራሩ ትኩረት ሰጥቶ ተግባሩን ማከናወን እንደሚገባዉ የተናገሩት ዋና አስተዳዳሪው፤ በተለይም የገቢዎች መምሪያ እና ንግድና ኢንዱስትሪ ልማት መምሪያ ቅንጅታቻውን አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው እንዲሁም ግብር ከፋዩ ማህበረሰብ ከመንግስት ጎን በመሆን የሚጠበቅበትን የዜግነት ግዴታ በአግባቡ መወጣት እንዳለበት መልዕክታቸዉን አስተላልፈዋል፡፡
የአሪ ዞን ገቢዎች መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ ታደለች ምክሬ በበኩላቸው፤ በበጀት ዓመቱ ከመደበኛ እና ማዘጋጃ ቤታዊ ገቢ 1.2 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ ግብር ከፋዩ ማህበረሰብ በአመቱ ማጠቃለያ በሚያደርገዉ የግብር ክፍያ የሚደርስበትን ጫና ለመቀነስ በየሩብ ዓመቱ የግብሩን 1/4ኛ እንዲከፍል በመደረጉ የበጀት ዓመቱ ሳይጠናቀቅ ከእቅድ በላይ ማሳካት መቻሉን ተናግረዋል፡፡
አክለዉም በ2018 ከ9 ሺ 42 በቀድሞዉ የደረጃ ‹ሐ› በአሁኑ የደረጃ ‹ለ› ግብር ከፋዩች በ10 ቀናት ውስጥ ቀሪ የአንድ ሩብ ዓመት ከ20 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ከዚህ ቀደም ከቴክኖሎጂ አጠቃቀም ጋር ተያይዞ የነበሩ ችግሮችን በመቅረፍ ሁሉን ያሳተፈ ስራ ለማከናወን መምሪያው በቂ ዝግጅት በማድረጉ እያንዳንዱ የሚመለከታቸዉ ባለድርሻ አካላት ከገቢ ተቋማት ጋር በመቀናጀት ከሐምሌ 1 ጀምሮ ግብርና ታክስ የመክፈል ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል አንዳለበት አሳስበዋል፡፡
የአሪ ዞን ንግድና ኢንዱስትሪ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ተመስገን ባይስማይ፤ በዞኑ የንግዱን ሥርዓት ከማዘመን ባለፈ ህገ-ወጥነትን ለመከላከል በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዉ የንግዱ ማህበረሰብ ከሐምሌ አንድ ጀምሮ ግብሩን በሚከፍልበት ወቅት የ2019 የንግድ ፍቃድ ምዝገባና እድሳቱን አብሮ እንዲያስኬድ አስፈላጊዉ ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡
የጂንካ ከተማ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዜዳንት አቶ ወንዱ ሻሆ፤ የንግዱ ማህበረሰብ እስከ ሐምሌ 10 ድረስ የ2018 የአንድ ሩብ ዓመት ቀሪ ግብራቸዉን በወቅቱና በታማኝነት እንዲከፍሉና የንግድ ፍቃዳቸዉን በማደስ የዜግነት ግዴታቸዉን እንዲወጡ ከሚመለከታቸዉ ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በመድረኩ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ፣ የዞኑ ዋና የመንግስት ተጠሪን ጨምሮ የመምሪያ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በዞኑ ዉስጥ ያሉ መዋቅሮችና ባለድርሻ አካላት የተገኙ ሲሆን የተለያዩ ሰነዶች ቀርበዉ ውይይት ተደርጓል።
ዘጋቢ፡ በናወርቅ መንግስቱ – ከጂንካ ጠቢያችን
የህብረተሰቡን የልማት ፍላጎት ለማሟላት ዞኑ የሚያመነጨውን ገቢ አሟጦ መሰብሰብ እንደሚገባ የአሪ ዞን አሰተዳደር አስታወቀ

More Stories
በጎፋ ዞን በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ1 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብስቡን የዞኑ ገቢዎች መምሪያ አስታወቀ
የሀዲያ ዞን ምክር ቤት 2.8 ቢሊየን ብር ተጨማሪ በጀት አጸደቀ
በበጀት አመቱ 98ሺህ 200 ቶን የኢንዱትሪ ማእድንና 13ሺህ 110 ቶን ሜትር ኪዩብ የኮንስትራክሽን ማእድን ማምረት መቻሉ ተገለጸ